የማኅበረሰባዊ እሴቶች መከበር የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንዳለው የፎክሎርና ሥነ ጽሑፍ መምሕር ብርሃን አሰፋ (ዶ.ር) አመላከቱ።

31

ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ ለዘመናት ሲተቀገር የዘለቀ ሁለት የተቃቃሩና የተጣሉ ወገኖችን የማሥማማት ሥርዓት ነው።

በአጥፊውና ተጎጅው ተግባብተውና የበደለ ካሳ ከፍሎ የሰላም ሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርግ ለሺህ ዓመታት የተሠራበት እሴት እንደኾነ አድማሱ ገበየሁ (ዶ.ር /ኢንጅነር) “መግባባት” በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ አስቀምጠዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአኗኗር ሥርዓቱ ለምዶትና አክብሮት የሚኖር የፍትሕን ጥያቄ የሚመልስበት ከማኅበረሰባዊ ባሕል እና ከሃይማኖቶች የተቀዳ ድንቅ የሀገር እሴት ነው። ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ ከኅብረተሰቡ ወግ፣ ልማድና ባሕል የተቀዳ፣ ሃይማኖታዊ መሠረት ጭምር ያለው በመኾኑ ተቀባይነቱ፣ ክብርና መታመኑም የላቀ እንደነበርም አስፍረዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎርና ሥነ ጽሁፍ መምሕር ብርሃን አሰፋ (ዶ.ር) ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች በኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊና ሰፊ መሠረት ያላቸው እሴቶች እንደኾኑ ለአሚኮ ተናግረዋል። በሀገሪቱ ከጥንት እስከ አሁን ግጭቶችን በመፍታት ቀዳሚ እና እንደ አንድ የመንግሥት ተቋም የግጭት መፍቻ ኾነው ማገልገላቸውንም ገልጸዋል።

ከሃይማኖታዊ እና ከማኅበረሰቡ አመጣጥ ጋር የተያያዙና በቅብብሎሽ እየተላለፉ የመጡ ጥንታዊ እና ችግርን በአስተማማኝ መንገድ ሲፈቱ የኖሩ እሴቶች በመኾናቸው የሚፈጸመው እርቅ ውጤታማና የጸና መኾኑንም አንስተዋል።
ለእርቁ መጽናት ምክንያቶቹ ደግሞ፦

👉 ወደ ግጭት መፍቻ ተቋማት የሚመጡት ሰዎች ጉዳያቸው የሚታየው በድብቅ፣ በጠበቃ፣ በአቃቤ ሕግ ወ.ዘ.ተ ሳይኾን ራሳቸው ፊት ለፊት ተቀራርበው ስለሚነጋገሩገ፣ በዳይና ተበዳይ ስለጉዳዩ ምንነት ጠንቅቀው እንዲረዱ ስለሚያደርግ፣

👉 አሸማጋዮቹ በማኅበረሰቡ ትልቅ ሥም እና በማስታረቅ ሰፊ ልምድ ያላቸው፣ ለእውነት የሚፈርዱ እና ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ተማምነው በጋራ የሚመረጧቸው መኾናቸው፣

👉 የግጭት መፍቻው በዘፈቀደ የተቋቋመ ሳይኾን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በመኾኑ በሁለቱ ወገኖች እምነት የተጣለበት መኾኑ፣

👉 አጥፊው የጉዳት ካሳ መክፈል ግዴታው መኾኑ፣
👉 ተሸማጋዮች እና አስታራቂ ሽማግሌዎች ወደ እርቅ ሲገቡ በመሃላ ስለሚገቡ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ በሀቅ ላይ የተመሠረተ ስለሚያደርገው፣

👉 በተከራካሪ ቡድኖች መካከል አሸናፊና ተሸናፊ የሚባል ነገር አይኖርም፤ እርቁ ሁለቱ ወገኖች የሚያጡትም የሚያገኙትም ነገር ላይ የተመሠረተ መኾኑ፤

👉 ሁለቱ ወገኖች እርቅ ከፈጸሙ በኋላ በማኅበረሰቡ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የእርቅ ማጽኛ ክዋኔዎች በወንዝ ዳር፣ ገደል አፋፍ ወ.ዘ.ተ. ላይ ይፈጸማል። እርቁ ሲጠናቀቅም እርቁ እንዳይፈርስ ማኋላ፣ ምርቃት፣ እገዳ በሚሉት መርኾዎች ስለሚከናወን የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

መምሕሩ እንዳሉት በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ መሪዎች ከዘመናዊ ትምሕርት ይልቅ መንፈሳዊ እና ሀገር በቀል እውቀቶችን የተማሩ፣ በእውቀታቸው እየተፈተኑ እና እየተገመገሙ ያለፉ በመኾናቸው ለማኅበረሰቡ ባሕል፣ ወግ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ትልቅ ዋጋ በመሥጠት ይታወቃሉ። ለዚህም አጼ ምኒልክን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ትኩረት ከሚሰጧቸው እሴቶች ውስጥ ደግሞ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ተጠቃሾች ናቸው።

አጼ ምኒልክ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ወቅት በሀገሪቱ የሚነሱ ግጭቶችን ለማርገብ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችን እንደዋነኛ መፍቻ መንገድ ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል።

ከጅማው ንጉስ አባ ጅፋር፣ ንጉስ ጦና እና ሌሎችንም የአካባቢ ገዥዎችን እና በጦርነት የማረኳቸውን ጭምር ከመቅጣት ይልቅ በሽምግልና፣ በድርድርና በእርቅ ችግሮችን መፍታታቸውን ነው መምሕሩ ያነሱት። በአንጻሩ የደርግ ሥርዓት ሶሻሊዝምን ሲያቀነቅን ከባሕልና ከእምነት ባፈነገጠ መንገድ በመጓዙ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ማጣቱንና ለውድቀቱም አንዱ ምክንያት እንደኾነ አንስተዋል።

አጼ ቴዎድሮስም ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የታተሩ ጠንካራ መሪ ቢኾኑም ሃይማኖታዊ እሴቶችን ባለማክበራቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶባቸው እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይም ችግሮችን በሽምግልና የመፍታት ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ተቋማት የሚጠቀሟቸውን ስልቶች መንግሥት ሙሉ በሙሉ ማክበርና መጠቀም እንደሚገባው ዶክተር ብርሃን አመላክተዋል።

በዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article24ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
Next article“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ ለመቀየር ያስችላል“ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በለጠ ሞላ ( ዶ.ር )