ጎብኚዎች ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እንዲመጡ ሰላም ወሳኝ መኾኑን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

108

ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጎብኚዎች እንዲመጡ ሰላም ወሳኝ መኾኑን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በድንቅ ተፈጥሮዊ ውበት የታደለው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል፡፡ በውስጡ የያዛቸው ብርቅዬ እንስሳት፣ ተፈጥሮ ያሳመራቸው ውብ ተራራዎችና ፏፏቴዎች የስሜን ብሔራዊ ፓርክን ተወዳጅ ያደርጉታል፡፡ ከዓመት እስከ ዓመት ያማረ ውበት የማይለየው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በክረምት ደግሞ ውበቱ ጎልቶ ይወጣል፡፡

በሀገራቸው የሚከሰተውን ከፍተኛ ሙቀት የሚሸሹ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የኢትዮጵያን የክረምት ወቅት ይመርጡታል፡፡ በክረምት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ደግሞ ወደ ስሜን ተራራዎች ያቀናሉ፡፡ በዚያውም ለረጅም ጊዜ ተፍጥሮን እያደነቁ ይቆያሉ፡፡ በየጊዜው በርካታ ጎብኚዎችን የሚጠብቀው የአካባቢው ማኅበረሰብ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ጎብኚዎችን ናፍቋል፡፡ ይህ የኾነው ደግሞ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ነው፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ክፍል ተወካይ ኀላፊ ላቀው መልካሙ ሰላም ያለ ቱሪዝም ምንም መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ በርካታ ጎብኚዎች ለመዳረሻነት እንደሚመርጡት የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው የኮሮና ቫይረስ እና ከትህነግ ጋር የነበረው ጦርነት የቱሪዝም እቅስቃሴውን ጎድቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የስሜን ተራራዎች በኢትዮጵያ ለቱሪዝም መዳረሻነት በቅድሚያ ከሚመረጡ የተፈጥሮ መዳረሻዎች መካከል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ በፊት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በዓመት እስከ 12 ሺህ ጎብኚዎች ይጎበኙት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ሊጎበኙ ከሚመጡት ጎብኝዎች መካከል 90 በመቶ የሚኾኑት የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በተፈጠረው ሰላም የቱሪዝም እንስቀሴው መነቃቃት አሳይቶ እንደበርም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት በርካታ ጎብኚዎች እንደጎበኙት የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው ወደነበረበት በመመለስ ላይ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት የቱሪዝም እንስቃሴውን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንዳቋረጠውም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ ጎብኚዎችን ይጠብቁ እንደነበርም ነው ተወካይ ኀላፊው የተናገሩት፡፡ ጎብኚዎች በስጋት ውስጥ ኾነው ወደ ቱሪዝም መዳረሻዎች እንደማይሄዱም ገልጸዋል፡፡ ለቱሪዝም አስተማማኝ ሰላም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ መሠረታቸውን በቱሪዝም እንቅስቃሴ ያደረጉ ዜጎች አሁን ላይ ሥራ አጥ ኾነው መቀመጣቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አስጎብኚዎች፣ በቅሎና ፈረስ አከራዮች፣ ድንኳን ተካዮችን ጨምሮ ቱሪዝም ላይ የተመሠረቱ ዜጎች ከሥራ ውጭ ኾነዋል ተብሏል፡፡የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አሁን ላይ እጅግ ውብ የሚኾንበትና በርካታ ጎብኚዎችን የሚስብበት ወቅት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይሄን ወቅት ይመርጡት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ በፓርኩ የተሻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በሚታይበት በዚህ ወቅት የተፈጠረው የሰላም እጦት ሊገኝ የሚችለውን ገቢ እንዳሳጣውም ገልጸዋል፡፡ ፓርኩ ከቱሪዝም የሚያስገኘው ጥቅም ሲቀር የፓርኩን ደኅንነት ለመጠበቅ አስቸጋሪ እንደሚኾን የተናገሩት ኀላፊው ማኅበረሰቡ ፓርኩን የሚጠብቀው የሚያስገኘውን ጥቅም በማሰብ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሲቀንስና የሚያስገኘው ጥቅም ሲቀር ካልተጠቀምን ምን ይሠራልናል በሚል ማኅበረሰቡ እንክብካቤውን እንደሚቀንስም ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ፓርኩን በዘላቂነት እንዲጠብቅና ጊዜያዊ ችግሮችን እንዲያልፍ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝም መቀዛቀዝ ከቱሪዝም የሚገኘውን ሀብት ማሳጣት ብቻ ሳይኾን የፓርኩን ደኅንነትም እንደሚጎዳው ነው የተናገሩት፡፡ ሁሉም ስለ ሰላም በመሥራት ሰላማዊ እንቅስቃሴውን መመለስ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተናገሩት ተወካይ ኀላፊው መንግሥት ችግሮቹን በአስቸኳይ ፈትቶ ጎብኚዎች እንዲመጡ እንዲያደርግ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር በአስቸኳይ ፈትቶ ጎብኚዎችን መሳብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ለአፍሪካም ኾነ ለዓለም እድገት መልካም ዜና ነው” ሎውረንስ ፍሪማን
Next articleአዴት ከተማ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡