“ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ለአፍሪካም ኾነ ለዓለም እድገት መልካም ዜና ነው” ሎውረንስ ፍሪማን

53

ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰውየው ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ መሻሻል እና እድገት ሳይታክቱ ምክረ ሃሳብ ያቀረቡ ምዕራባዊ የኢትዮጵያ ወዳጅ ናቸው፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጧ ድረስ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ ሲሞቅ የሚሞቁ ሲቀዘቅዝ ደግሞ የሚቀዘቅዙ የልብ ወዳጅ ናቸው ይባልላቸዋል፤ እውቁ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን፡፡

ብሪክስ የተንሸዋረረውን ምዕራብ ዘመም የምጣኔ ሃብታዊ ስሪት ሚዛን ለማስጠበቅ ፍቱን አማራጭ ኾኖ ቀርቧል የሚሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ በተለይም ከሀገራቱ ባሕል ውጭ በሚቀርቡ የፖሊሲ ሰበቦች የብድር እና እርዳታ አማራጮች ተነፍገዋቸው ለቆዩ ታዳጊ ሀገራት እጅጉን አስፈላጊ ነበር ይላሉ፡፡ አፍሪካ እጅግ በርካታ የማደግ ተስፋ እና አማራጮች ያሏት አሕጉር ብትኾንም ለዘመናት ከውስጥም ከውጭም የኾኑባት አዎንታዊ ነገሮች እድገቷን ገትተው የምዕራቡን ዓለም ድጋፍ አጥብቃ የምትሻ ኾና ቆይታለች ይላሉ፡፡

በርካታ የአሕጉሪቷ ሀገራት አምራች የሰው ኀይል፣ እምቅ ተፈጥሯዊ ሀብት እና ያልተነካ ጥሬ እቃ ያሏት ባለፀጋ አሕጉር ናት የሚሉት ፍሪማን ከቅኝ ግዛት እስከ ዘመናዊ ባርነት ያሳለፈቻቸው ወረራዎች ክፉኛ ደቁሰዋት አልፈዋል ነው ያሉት፡፡ ከድህረ ዘመናዊነት እና ሉላዊነት ማግስትም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እና ሀገራት ለአሕጉሪቷ ዓሳን ከባሕር እንዴት ማስገር ሳይኾን ዓሳን የመመገብ መርህን ብቻ መከተላቸው ለውጥ አልባ አድካሚ ጉዞን እንድታሳልፍ እንዳደረጋት ያነሳሉ፡፡

የዛሬ 15 ዓመታት ገደማ የተቋቋመው የምጣኔ ሃብት እና ትብብር አማራጭ ተቋም ብሪክስ በፖሊሲ ሰበብ ብድር እና ድጋፍ ተነፍገው ለተቀፈደዱ ሀገራት ተስፋ ይዞን መጥቷል ይላሉ፡፡ በተለይም ተቋሙ በአምስት ዓመታት ቆይታው ብቻ የራሱን ባንክ ማቋቋም መቻሉ የድሀ ሀገራት ዐይን ማረፊያ ኾኗል ነው የሚሉት፡፡ ብሪክስ ከሰሞኑ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ኢትዮጵያን አባል አድርጎ ማካተቱ እንዳስደሰታቸው ፍሪማን ከሀገሪቷ ሚዲያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ለአፍሪካም ኾነ ለዓለም እድገት መልካም ዜና ነው” የሚሉት ሎውረንስ ፍሪማን ላለፉት 10 ዓመታት ደጋግሜ ስናገረው የነበረው ይኽንን መሰሉን ተራማጅ ለውጥ ለማየት ነበር ብለዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ብሪክስን መቀላቀላቸው ለአሕጉሪቷ ትልቅ ውክልና መኾኑንም የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ይናገራሉ፡፡ ብሪክስ ጅማሮውን አጠናክሮ በመቀጠል የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትንም በአባልነት ለማካተት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

ከ11 የብሪክስ አባላት ሀገራት መካከል ሦስቱ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው የሚሉት ፍሪማን ሦስቱ ሀገራት የብሪክስ አባል ሀገራትን 30 በመቶ የሕዝብ ብዛት ይሸፍናሉ ብለዋል፡፡ ይኽም ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ አቅም መኖሩ እንደ ትልቅ ድልም እድልም የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ ብሪክስ ራሱን አንድ የምዕራቡን ዓለም የፖለቲካል ኢኮኖሚ እንደሚገዳደር አማራጭ ተቋም በማየት አማራጮችን ማስፋት እና ኀይልን ማሰባሰብ ይገባዋል ብለዋል ፍሪማን፡፡

ብሪክስ የአፍሪካ ሀገራትን በአባልነት በስፋት ሲያካትት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የብሪክስ መሪዎች እና የዓለም ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ዘዋሪዎች እንደኾኑ ማመን ይገባዋል፡፡ የብሪክስ ልማት ባንክ የብድር ተደራሽነቱን በማስፋት ላይ ይገኛል ያሉት ሎውረንስ ፍሪማን 30 በመቶ የሚኾነው አዲስ የብድር አቅርቦት ከሀገራቱ የውስጥ ምንዛሬ የሚሸፈን ይኾናል ነው ያሉት፡፡ ፍሪማን አክለውም የአፍሪካ ሀገራት ከዓለም ባንክ እና ከዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) ብድር ለማግኘት የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በመቀነስ አላስፈላጊ ጫናዎችን ይቀንስላቸዋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለደብረሲና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ።
Next articleጎብኚዎች ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እንዲመጡ ሰላም ወሳኝ መኾኑን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡