
ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አመራሮች እና ሠራተኞች የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2016 ዓ.ም እቅድ ትውውቅም አድርገዋል። የቢሮ ኀላፊው አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት ባለፈው የ2015 በጀት ለአርሶ አደሩ የባለቤትነት ዋስትና የሚሆን አረንጓዴ ደብተር የመስጠት ሥራ በሰፊው መከናዎኑን ተናግረዋል። ከባንኮች እና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የጋራ ምክክር በማድረግ በአረንጓዴ ደብተር ማስያዣነት አርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾን መሠራቱንም ገልጸዋል።
የገጠር መሬት በዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ተመዝግቦ የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የመስጠት ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመልካም ተሞክሮነት የሚያዝ ቢኾንም የከተማ መሬት ይዞታን ከማረጋገጥ አኳያ ግን ውስንነቶች ነበሩ ተብሏል። የዚህም ምክንያቱ የባለይዞታዎች የሕግ ግንዛቤ እና የተቀላጠፈ ቅንጅታዊ አሠራር ውስንነት መኖሩ ነው ሲሉ አቶ ሲሳይ ተናግረዋል። በከተማ መሬት አገልግሎት የግል ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ ብልሹ አሠራርን የተላበሱ አንዳንድ ባለሙያዎች መኖራቸውም የተፈለገውን ያህል ሥራ ለማከናዎን እንቅፋት ነበሩ ብለዋል።
ቢሮ ኅላፊው በ2016 ዓ.ም የመሬት ነክ አገልግሎትን ለማሻሻል ታልሟል ነው ያሉት። “መሬት ነክ አገልግሎት የእጅ መንሻ ከሚጠይቁ ባለሙያዎች የጸዳ እንዲኾን በትኩረት ይሠራል” ሲሉም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል። ለባለይዞታዎች እና ከመሬት ቢሮው ጋር ለሚሠሩ አካላት በጉዳዩ ላይ የሕግ ማዕቀፍ ስልጠናዎችን በማመቻቸት ተገቢውን የከተማ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የመስጠት ሥራ ይከናወናልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡-አሜናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!