
ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን እንደሚያጠናክር ቻይናውያን ፕሮፌሰሮች ገለጹ።
በቻይና ሬንሚን ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰርና የኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል ኅላፊው ፕሮፌሰር ሁአንግ ያንዣ የብሪክስ ስብስብ ለታዳጊ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ብሪክስ በርካታ የመሰረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች የልማት ዕቅዶች ያሉት እንደመሆኑ አዳዲስ አባል ሀገራት ከዚህ ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ብሪክስ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ባካሄደው 15ኛው ጉባኤ ኢትዮጵያ ጥምረቱን እንድትቀላቀል መወሰኑ ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።
እንደ ምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የምጣኔ ሃብትና ልማት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛታል ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የብሪክስ አባል የሆኑት ብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ግዙፍ ምጣኔ ሀብትና ሰፊ የህዝብ ቁጥር እንዳላቸው የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ ይህም ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጥምረቱን በመቀላቀሏ በመንግስታትና ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ይበልጥ እንደሚያሻሽልም ነው ያብራሩት።
የብሪክስ አዲስ የልማት ባንክ ለአባል ሀገራት በቀጥታ የተሻለ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል ስለመሆኑም አንስተዋል።
ፕሮፌሰር ያን ዣ ጥምረቱ የቻይና ኩባንያዎች የብሪክስ አባል ሀገራትን ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው እንዲያደርጉ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በማንሳት፤ መንግስት የትብብር መስኮችን በአግባቡ በመለየት ያለውን ዕድል ለመጠቀም ይበልጥ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰሩ አክለውም ኢትዮጵያ በርካታ የህዝብ ቁጥርና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል ያላት አገር በመሆኗ በርካታ የስራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማተኮር ጠቃሚ እንደሆነም መክረዋል።
በቻይና የሚንዙ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ጥናት ፕሮፌሰር ሂዮንግ ሂ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታሪክ በጣም ትልቅ ሀገር እንደሆነች በማንሳት፣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥም ከቀደምት አባቶች የስልጣኔ ስራዎች መማር እና ከሌሎች ሀገሮች ልምድ መቅሰም እንደሚገባት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊና ብዝኃ ማንነት ያላቸው ህዝቦችን ያቀፈች መሆኗም በብሪክስ አባልነቷ የጋራ ልማትና ዕድገትን ለማምጣት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በደቡብ ደቡብ የትብብር ማዕቀፍ አካታችና ፍትሐዊ የዓለም ስርዓትን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መግለፃቸው ይታወቃል።
በ15ኛው የብሪክስ ጉባኤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ግብፅ እና አርጀንቲና የጥምረቱ አባል እንዲሆኑ መወሰኑም ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!