
ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የግብርና ውጤት የኾኑ ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ ያለቀለትን ምርት ደግሞ በውድ ዋጋ ወደ ሀገር ውስጥ ስታስገባ ቆይታለች፡፡ በተለይ ደግሞ የቁም እንስሳትን እና የግብርና ውጤት የኾኑ እንደ ሰሊጥ እና የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ትታወቃለች፡፡
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግነኙነት ኀላፊ ይኸነው ዓለም እንዳሉት የአማራ ክልል ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡
በተለይም ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮችን (ቡሬ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ባሕር ዳር እና አረርቲ) በማልማት ባለሃብቶች እንዲገቡ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚሕም በ2012 ዓ.ም ወደ ውጭ ይልኩ ከነበሩ 18 ኢንዱስትሪዎች አኹን ላይ ወደ 36 አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ዘጠኝ የግብርና ምርት ላኪዎች ማድረስ ተችሏል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ከ80 ሺህ ቶን በላይ ምርት ወደ ውጭ በመላክ 139 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል፤ የዕቅዱንም 87 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ በተለይም ደግሞ ያለቀላቸው ቆዳዎችን፣ የጨርቃጨርቅ ውጤቶችን እና አበባ፣ አቮካዶ፣ እንጆሪ፣ ፕሮቲን ፓውደር እና የመሳሰሉ የግብርና ውጤቶችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት መላኩን ነው ኀላፊው ያነሱት፡፡
በክልሉ አምራች ፋብሪካዎችን ከማሳደግ ባለፈ የማምረት አቅማቸውን ማሻሻልና አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ክልል እንዲገቡ እየተሠራ መኾኑንም ነግረውናል፡፡
በክልሉ የሚስፋፉ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ በሥራ እድል ፈጠራ፣ ለአካባቢው ማኀበረሰብ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት እና ለቴክኖሎጅ ሽግግር ሚናቸው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይኹን እንጅ በክልል የተከሰተው ችግር በአምስት የግብርና ኢንቨስትመንቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አሳጥቷል፤ ሌሎች ባለሃብቶችን ለመሳብ ስጋት ፈጥሯል እንዲኹም ከ3 ሺህ በላይ ሠራተኞችም ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በክልሉ የሚስፋፉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ጠቀሜታቸው ለአካባቢው ማኅበረሰብ በመኾኑ ማኅበረሰቡ እንደ ራሱ ሃብት ሊጠብቃቸው ይገባል ብለዋል የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!