“ታሪክ ነጋሪ ጥንታዊ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ማኅበረሰቡ የትውልድ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

60

ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በየዘመኑ የሰውን ልጅ ሥልጣኔንና ዝማኔን ፣ ባሕል ፣ ወግና ሥርዓትን የሚዘክሩ የታሪክ አምባዎች ባለቤት ፤ ድንቅ የተፈጥሮ መልክዓ ምድር ትዕይንት መገኛ፤ የበርካታ የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለጸጋ ነው፡፡

ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ለቱሪዝም ዘርፉም ሀገራዊ አሻራው ከፍ ያለ ነው፡፡ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶችም መገኛቸው አማራ ክልል ቀድሞ ተጠቃሽ ነው፡፡

የሥልጣኔ አሻራ ማሳያዎችን የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስትያናትን ፣ ፋሲል ግቢና ሌሎች የጎንደር ሐውልቶችን ፤ በድንቅ ተፈጥሮም የሠሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የዓለም ቅርስ በማድረግ ረገድ አበርክቶውን ልብ ይሏል፡፡

በእርግጥም ክልሉ በየአካባቢው የጥንት ኢትዮጵያውያን የኪነ ሕንጻ አሻራ ማስታወሻ የኾኑት ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤት ነው።

ጉዳዩ ሰው ሠራሽም ኾነ ተፈጥሮዊ ፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም መዳረሻ፣ የባሕል፣ ወግ፣ ሥርዓት ፣ ሥነልቦና ፣ የሥልጣኔ አሻራ ምስክር፣ የትውልድ ኩራትና ሃብት የኾኑ ቅርሶቻችን የሚጠበቁበትና ያሉበት ኹኔታ የሚያሳስብ መኾኑ ነው፡፡ በእንክብካቤና ጥበቃ ምክንያት ጉዳትን እያስተናገዱ ለስርቆት ፣ ለብልሽትም እየተዳረጉ ነው ፤ ተደጋግሞ የሚነሳው ቅሬታ ነው፡፡

በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ ከአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት በክልሉ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች በተፈጥሮም ኾነ በሰው ሠራሽ ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል ብለዋል፡፡

በግንዛቤ እጥረት ፣ በጥበቃና እንክብካቤ ማነስ፣ በትኩረት ማነስ የሀገር ሃብት ፣ የትውልድ ኣሻራዎች ታሪካዊ ቅርሶች ጉዳትን እያስተናገዱ ነው፡፡

እየደረሰባቸው ያለውን ጉዳት ለመታደግ ክልሉ የቅረስ የጥበቃ ፣ጥገናና እንክብካቤ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ጋሻዬ በገንዘብ፣ በዕውቀትና ክህሎት ከአቅም በላይ ለኾኑ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ቅርሶቹን ከጉዳት የማዳን ተግባር ከፌደራል መንግሥት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ ካለው ሰፊ የቅርስ ሃብት እንክብክብካቤና ጥበቃ አንጻር በሚፈለገው ልክ መድረስ አልተቻለም። ቅርሶችን የማዳን ሥራውም በሚፈለገው ልክ አይደለም ነው የሚሉት፡፡

“ታሪክ ነጋሪ ጥንታዊ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት በኩል ሁሉም ዜጋ የትውልድ ኃላፊነቱን ይወጣ” መልእክታቸው ነው፡፡

ቅርሶቻችን አንዴ ከጠፋ ድጋሜ የማይገኙ የትውልድ ውድ ሃብቶች ናቸውና ሁሉም ሰው የጥንታዊ ቅርሶች ጠባቂ ፣ ተንከባካቢና ባለቤት ነኝ የሚል መንፈስ እንዲፈጠር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በሥፋት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሸው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት ውስጥ 98 በመቶው በምርት መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next articleበ2015 በጀት ዓመት ወደውጭ ከተላኩ ምርቶች 139 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ፡፡