በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት ውስጥ 98 በመቶው በምርት መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

64

ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015/16 የምርት ዘመን በዞኑ ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ በዞኑ ያለው ምቹ የክረምት ወቅት እና ተስማሚ የዝናብ ስርጭት ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስችል አቅም መፍጠሩንም መምሪያው አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል መንግሥት ትርፍ አምራች ከኾኑ አካባቢዎች መካከል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በተለይም ለገቢያ ተኮር የግብርና ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ቢኾንም ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን የተስተዋለው የገበያ ትስስር ችግር ለተያዘው የምርት ዘመን ስጋት እንደፈጠረም ተነስቷል፡፡

በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከሚለማው 561 ሺህ 685 ሄክታር መሬት ውስጥ 550 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር ምርት እርሻ መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኅላፊ አወቀ መብራቱ አስታውቀዋል፡፡ በመኸር እርሻ የተሸፈነው መሬት ከዕቅዱ 98 በመቶ ይሸፍናል ያሉት መምሪያ ኅላፊው ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

በዞኑ በርሃማ አካባቢዎች የሰሊጥ ፣ ማሽላ እና ጥጥ ምርቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየለሙ መኾኑን ያወሱት ኅላፊው በደጋማው የዞኑ አካባቢዎች ደግሞ በጤፍ ፣ በበቆሎ ፣በዳጉሳ እና በአተር ምርቶች ተሸፍኗል ተብሏል፡፡ በዞኑ ያለው ተስማሚ የዝናብ ስርጭት እና ምቹ የክረምት ወቅት መኖር የታቀደውን ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል እድል መፍጠሩንም አቶ አወቀ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በዞኑ ጥጥ ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ በሰፊው ቢመረትም የገበያ ትስስር ባለመኖሩ አምራቾች ያመረቱት ምርት አሁንም በመጋዘን ውስጥ ይገኛል ያሉት ኅላፊው በተያዘው የምርት ዘመን ተመሳሳይ ምርቶችን ለማምረት ስጋት ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ካለፈው ዓመት የገበያ እጥረት ስጋት በመነሳት በምርት ዘመኑ ለሰሊጥ ፣ጥጥ እና የማሽላ ምርቶች ሰፊ ትኩረት ተሰጥቷል ነው የተባለው፡፡

በዞኑ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት የዛፍ አምበጣ ክስተት ሊፈጠር እንደሚችል ስጋቶች አሉ ያሉት አቶ አወቀ ክልሉ የኬሚካል እና የባለሙያ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቧል ብለዋል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ የዞኑን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ እያደረገ ያለው ያላሰለሰ ድጋፍ እና ክትትል ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረም አቶ አወቀ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
Next article“ታሪክ ነጋሪ ጥንታዊ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ማኅበረሰቡ የትውልድ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ