የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

73

ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክረምቱ ወራት የተጀመረው የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቆ የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

ዞኑ በትምህርት ዘመኑ 115 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ አቅዷል፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የ2016 ዓ/ም የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ገብረማሪያም መንግሥቴ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ማሻሻል፣ የመማሪያ ክፍል ጥገና፣ የትምህርት ግብዓት ማሟላት እና መሰል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ኅላፊው፤ ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ 197 የመጀመሪያ ደረጃ እና 22 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ ያሉት አቶ ገብረ ማሪያም፤ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምዝገባ ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ ነበር ብለዋል፡፡ በቅርቡም ሁሉም መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች በየትምህርት ቤቶቻቸው እንዲገኙ የተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ ምዝገባ መጀመሩን ነው የነገሩን፡፡

በትምህርት ዘመኑ 99 ሺህ 925 የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች እና 14 ሺህ 884 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ መታቀዱንም ኃላፊው አንስተዋል፡፡

የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት ከማዕከላት ወደ ትምህርት ቤቶች መጓጓዝ መጀመሩን የነገሩን ኃላፊው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዞኑ ቅድሚያ ሰጥቶ ያደረገው ድጋፍ አበረታች ነበር ብለዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ትምህርት ቤቶችን በትምህርት ግብዓት ማገዝ፣ ቁሳቁስ ማሟላት እና መሰል ድጋፎችን ማድረግ ከባለሃብቱ እና ከአካባቢው ተወላጆች ይጠበቃል የሚሉት አቶ ገብረ ማሪያም የትምህርት ግብዓት ማሟላት የማይችሉ ተማሪዎችን መደገፍም የቀጣይ ጊዜ ሥራ ይኾናል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካ ሲንጋፖር ቢዝነስ ፎረም 2023 በሲንጋፖር መካሄ ጀመረ።
Next articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት ውስጥ 98 በመቶው በምርት መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡