
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባገጠመው የጸጥታ ችግር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ያቋረጡ ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት መጨረሱን የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሐምሌ 19 እስከ 30/2015 ዓ.ም ድረስ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናቸውን ሳይጨርሱ ከዩኒቨርሲቲ ወጥተዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የሀገር አቀፍ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የመጨረሻ ፈተናዎችን ሳይወስዱ መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ፈተናቸውን ያልወሰዱ ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈተኑ እየተሠራ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ የሰላም ኹኔታው ባለበት መሻሻል ከቀጠለ በመስከረም ሁለተኛው ሳምንት ገደማ ፈተናውን ለመስጠት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ከሰላም እጦቱ ድባብ ወጥተው አስፈላጊውን የሥነ ልቦና ዝግጅት አድርገው እንዲፈተኑ መምህራን፣ ወላጆች እና መላው የትምህርት ማኅበረሰብ ድጋፍ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል፡፡ ተማሪዎችን ለማስፈተን ከትምህርት የሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ማንጠግቦሽ አዳምጤ የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሁልጊዜ በተሻለ መልኩ ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በጎንደር ዪኒቨርሲቲ ሲፈተኑ የነበሩ ተማሪዎች ፈተናቸውን ሳይጨርሱ መውጣታቸውን ነው የገለጹት፡፡
የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የመጨረሻዎቹን ፈተናዎች ሳይፈተኑ መቋረጡንም አስታውቀዋል፡፡ ተቋማቸው ፈተናዎችን በማዘጋጀት ፈተናውን ያልጨረሱ ተማሪዎች ፈተና እንዲወስዱ ዝግጅት መጨረሱንም ተናግረዋል፡፡ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል አስተማማኝ ደኅንነት እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል፡፡
አስተማማኝ ደኅንነት እና መረጋጋት እንዲኖር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረትና ርብርብ እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ፈተናቸውን እንዲወስዱ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎችም ፈተናቸውን ለመውሰድ ዝግጁ መኾን እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በተፈጠረበት ጊዜ ሁሉ መስጠት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!