
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሀንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ የተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ እንደወትሮው ኹሉ ከፍ ብሎ የተውለበለበበት መድረክ ነበር፡፡ ከድሉ ባሻገር የነበረው የቡድን ሥራ ኢትዮጵያዊያንን ኹሉ ያኮራ ነበር፡፡
“አረንጓዴው ጎርፍ” እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፤ ዘንድሮ ስያሜውን በሚመጥን መልኩ አትሌቶቻችን ተከታትለው በመግባት የሀገራችንን የድል ታሪክ ደግመዋል፡፡
በተለይ ሴቶች አስር ሺህ ሜትርና በማራቶን ሩጫ የታየው የቡደን ሥራ፣ እርስ በእርስ መናበብ እና መረዳዳት ከድል ምክንያትነቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊያን ስንተባበር ተአምር መሥራት እንደምንችል አመላካች ነበር፡፡ አትሌቶቻችን በሩጫ ወቅት መረጃ በመለዋወጥ፣ በመተጋገዝ እና አንዳቸው ሌላውን በመጠበቅ እስከመጨረሻው ድረስ በቡድን ተጉዘዋል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ በሩጫ ላይ አትሌቶቿ ባሳዩት መተባበርና መተጋገዝ ተምሳሌት መኾኗን ዳግም ያሳየ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል፡፡
ሀገራችን በጠቅላላ ውድድሩ ኹለት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሦስት የነሀስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ኹለተኛ ኾና ውድድሩን አጠናቅቃለች፡፡ ጥሩ ውጤት ያስመዘገብንባቸዉም ሆነ በተሳተፍንባቸው ውድድሮች በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ስንቅ የሚኾኑ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል፡፡
በዋናነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአትሌቲክስ ውድድሮች ጠፍቶ የነበረው የኢትዮጵያዊያን የቡድን ሥራ በዘንድሮው ውድድር በጉልህ መታየቱ በዘርፉ ያለንን ስኬት በቀጣይ ጊዜያት ለማሻሻል የሚያስችል እንደኾነ ይታመናል፡፡ ከምንም በላይ ከውጤቱ ባሻገር ውጤቱ የተገኘበት መንገድ ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ያስደሰተ፤ የሀገራዊ አንድነታችን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ አኩሪ ድል ነው፡፡
ሀገርን በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች በመወከል ድል ማስመዝገብ የሚወደስ ተግባር ነው፡፡ ሀገራችን ከጊዜያዊ አሉታዊ ፈተናዎች ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች ድል የሚያደርጉ የትጉሀን ሀገር መኾኗን ለዓለም ማሳየት በኹሉም ዘርፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በጥረታቸው ድል የሚያደርጉ፣ የሀገራቸውን መልካም ገፅታ አጉልተው የሚሳዩ የብርቅዬ ልጆች ቤት መኾኗ ዛሬም በዓለም አደባባይ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከፈተናዋ በላይ ተስፋዋ የለመለመ፣ አዎንታዊ ስኬቷም በእጅጉ እንደሚልቅ በተለያዩ ዘርፎች እየታየ ነው፡፡
በስፖርት ዘርፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የቀጠለው የአሸናፊነት ገድል በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው አካላት ኹሉ እንደተለመደው በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በየዘርፉ ድል ማድረጓን ትቀጥላለች!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!