
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ግጭትና ጦርነት ሰው በሰው ላይ የሚፈጽውም የእልቂት፣ የውድመትና የጉስቁልና መንገድ ነው።
ግጭትና ጦርነት በቀጥታ ከሚያደርሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪም በተዘዋዋሪ የሚያደርሰው የተራዘመ ማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው። በተለይም በጦርነቱ ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና መቃወስና የአእምሮ ጤና መቃወስ የሚያደርሰው ጉዳት አደገኛ እንደኾነ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያስረዱት።
ዶክተር አማረ ዓለምወርቅ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህር ናቸው። በጦርነት ወቅት በኅብረተሰቡ በግጭት ከሚደርሰው ጉዳት ባሻገር በሥነ ልቦናዊ መቃወስ የሚጎዳው የኅብረተሰብ ቁጥር ቀላል አይደለም ብለዋል ከአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃ የሚጠቅሱት ዶክተር አማረ በጦርነትና ግጭት ተጎጂ በኾኑ አካባቢዎች ከሚኖሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች 10 በመቶው ከፍተኛ ለኾነ የረጅም ጊዜ የአእምሮ ጤና መቃወስ ጉዳት ይዳረጋሉ ይላሉ።
በጦርነትና ግጭት ወቅት የሚለቀቅ መረጃና የመረጃ አጠቃቀም ለማኅበራዊ ቀውስና የአእምሮ ጤና መቃወስ መፈጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው ባለሙያው የሚያስረዱት።
ለአእምሮ መቃወስ ከሚያጋልጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ታዲያ በቀጥታ የጉዳቱ ሰለባ ከሚኾኑት በተጨማሪ በግጭቱና በጦርነቱ የደረሰውን ጥቃትና ውድመት በመስማት እና በማየት ለአእምሮ መረበሽ ይዳረጋሉ ነው የሚሉት። በተለይም ጦርነቱ ወይም ግጭቱ ያደረሰውን ውድመት፣ ሞት ፣ እልቂት፣ እንዲሁም በቀጣይ ሊያስከተትል የሚችለውን ጥቃት በመስጋት፣ ነገ እኛም የዚሁ ግጭትና ጦርነት ሰለባዎች እንኾናለን በሚልም ጭምር ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በመሥማት እና በማየት ለአእምሮ መቃወስ ይዳርጋሉ ብለዋል።
በግጭትና ጦርነት በሚታመስ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጭንቀት ፣ ድብርት ፣ ፍርሀት ፣ የአእምሮ እረፍት ማጣት እና የእንቅልፍ ማጣት ከልክ በላይ እየተባባሰባቸው ይመጣል፤ ለከፍተኛ የአእምሮ መቃወስም ይዳረጋሉ ብለዋል በሰጡት ማብራሪያ። በዚህ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች የማሰብ አቅማቸው ይቀንሳል፤ መጥፎ የባህሪ ለውጥም ያጋጥማቸዋል ዶክተር አማረ እንደሚሉት።
በጦርነት ፣ ግጭትና ብጥብጥ በማያባራበት ሀገር ወይም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቢያንስ እንኳን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመጣን የአእምሮ መቃወስ ለመከላከልና ለመቀነስ መሥራት አለባቸው ይላሉ።
ዶክተር አማረ እንደሚሉት :-
👉 የመረጃ አጠቃቀማቸውን ልክ መለየትና መረጃን መምረጥ።
👉 ከዕውቀታቸው ፣ ከእድሜያቸውና ከግንዛቤያቸው በላይ የኾነን መረጃ አለመጠቀም።
👉 ከግንዛቤ በላይ የኾነ መረጃን በመተንተን “ይኾናል አልያም እየኾነ ነው” በማለት ከመረበሽና ከመጨነቅ መራቅ።
👉 በተለይም ልጆች ከእድሜና ከአቅማቸው በላይ የኾነን የጥፋት መረጃ ማየት የለባቸውም ፤ ወላጆች የመጀመሪያውን ኀላፊነት ሊወስዱ ይገባል።
👉 መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ፤ የለቀቁት መረጃ ከጥቅሙ ይልቅ የሚያደርሰውን ጉዳት መረዳት ፣ መመዘን ይኖርባቸዋል።
እናም ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ከመሥራትም ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ እራሱንም ከተበከለ መረጃና ለአእምሮ ጤና መቃወስ ከሚያጋልጥ ኹኔታ መጠንቀቅ ይኖርበታል ብለዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!