
ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እ.ኤ.አ በ2020 በኢትዮጵያ በፀጥታ ችግርና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማስቀጠል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ጋር በመነጋገር ስምምነት ላይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመጡ ተወካዮችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አፈፃፀም ሥምሪት ላይ ተወያይተዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በተ.መ.ድ. አመራሮች መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማስቀጠል በፖሊስ ዩኒቨርስቲ የቅድመ ስምሪት ስልጠና የወሰዱ የፖሊስ መኮንኖችን ብቃት ለመመዘን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል።
ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከክልል እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ እንዲሁም ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የተውጣጡ የፖሊስ መኮንኖች የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ምዘና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!