
ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአጣየና አካባቢዉ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በወጥነት ለማስቀጠል የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል በአካባቢዉ የተቋቋመዉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ብርጋዴር ጀነራል እሸቱ መንግሥቴ።
ጀኔራል መኮንኑ ይሄን ያሉት የኤፍራታና ግድም ወረዳ እና የአጣ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞችን ማዕከል ያደረገ ዉይይት በአጣዬ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነዉ፡፡ በአማራ ክልል ለተፈጠረዉ ሁሉን አቀፍ ችግር መፍትሔ ማምጣት የሚቻለዉ ሁሉም በቀናነት ለመፍትሔዉ ሲተባበር መኾኑም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በየደረጃዉ የሚገኘዉ የመንግሥት ሠራተኛ መፍታት የሚችለዉን የመልካም አሥተዳደር ችግር በመፍታት በጥቅል ለሚነሳዉ ጥያቄ አጋዥ ይኾናል ተብሏል፡፡ በዉይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የመንግሥት ሠራተኞችም አሁን ላይ በከተማቸዉ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ አንስተዋል፡፡ ይህንን ዘላቂ ለማድረግ የበኩላቸዉን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አሳልፍ ደርቤ የመንግሥት ሠራተኛዉ የተለመደዉን መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ በመኾኑም በሁሉም መስሪያ ቤቶች ያሉ ሠራተኞች በመደበኛ ሥራቸዉ ላይ ተገኝተዉ ሥራቸዉን እንዲከዉኑም አሳስበዋል፡፡
በአካባቢዉ የተቋቋመዉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ብርጋዴር ጀነራል እሸቱ መንግሥቴ አካባቢው ሰላም እንዲኾን ሕዝቡ እያደረገ ያለዉን ትብብር አድንቀዋል፡፡ አሁን ላይ እየታዬ ያለዉን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠልም የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ሠራዊቱ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ኀላፊነቱን በቁርጠኝነት እየተወጣ ነዉም ብለዋል፡፡
አካባቢዉ ለበርካታ ጊዜያት ለችግር ሲዳረግ መቆየቱን ያነሱት ጀነራል መኮንኑ በችግር ላይ ችግር እንዳይደራረብ ለማድረግ ሰላም ላይ አጥብቀን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ያለዉን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!