“ከእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ዘርፍ የሚገኘው ጥቅም በሰላም እጦት ምክንያት ዳግም እንዳይፈተን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” የአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት

72

ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በርካታ የእንስሳት ሃብት ክምችት ያለበት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ያለው ክልል ነው ይላሉ የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዳዊት ገዳሙ።

የክልሉን ሃብት አልምቶ አርሶ አደሮችም ኾኑ የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ልማት፣ መከላከልን መሠረት ያደረገ የእንስሳት ጤና ቁጥጥር ሥራ ላይ ሠፊ አገልግሎት ሲሠጥ መቆየቱን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

ለክልሉ ከሚቀርበው ወተት ፍጆታ በተጨማሪ ከ230 ሺህ ሊትር በላይ ወተት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ይላክ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በክልል የተከሰተው አለመረጋጋት በየቀኑ ከአርቢዎች የሚሰበሰበው ወተት የሚጓጓዝበት መንገድ ዝግ በመኾኑ ለብልሽት እየተዳረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

የወተት፣ የሥጋ፣ የማር እና የእንቁላል ምርትን ለማሳደግ የመኖ ልማቱ ቅድሚያ የሚሠጠው ቢኾንም ክልሉ ለእንቅስቃሴ ባለመመቸቱ ለመኖነት የተተከሉ የሣር ዝርያዎች ዩሪያ አልተጨመረባቸውም ብለዋል፡፡ የዶሮ መኖ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ አይቻለም፤ ምርቱንም ለፈላጊው የማቅረቡ ኹኔታ የተቀዛቀዘ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

የተገዛውን መኖ የተመገቡ ከብቶች የታለበው ወተት ለሽያጭ ባለመቅረቡ በአምራቹ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን አንስተዋል፡፡

የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት በዘርፉ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የንብ ሃብት ልማቱን ለማሻሻል የቀሰም ዕጽዋትን መትክል፣ ለድቀላ የሚያገለግሉ ላሞችን መምረጥ፣ ንቦችን መቅዳት ወይም መገልበጥ ቀዳሚ ተግብር ነው የሚሉት አቶ ዳዊት በዚህ ወቅት የሚሠሩ ሥራዎች ቢኾኑም ማከናዎን አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ አለመቻሉንም ያነሳሉ። እነዚህ ሥራዎች በወቅቱ ባለመሠራታቸው በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ለሰላሙ በጋራ እና በርብርብ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በወቅቱ ሥራዎች ባለመሠራታቸው ዘርፉ ለኪሳራ መጋለጡን ጠቁመዋል፡፡ ሰላም የኹሉም መሠረት ነው የሚሉት ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ሁሉም አካል ሰላም እንዲመጣ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰላም በሌለብት ውጤታማ ሥራ መሥራት፤ የተዋጣለት ወይም የተመረጠ ምርት ማምረት፤ የተሻሻለ የኢኮኖሚ አማራጭ ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ ለሰላም ቅድሚያ መሥጠት ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት በውስን መሬት እና በውስን ካፒታል ብዙዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘርፍ በመኾኑ መሠናክሎች በመቅረፍ ለሰላም የሚደረገው ሩጫ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠሪያ የኾነው የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ራሱን ችሎ ለመቆም ብዙ ፈተናዎች እንዲጋረጡበት ያደረገው የክልሉ አለመረጋጋት ወደቀደመ ኹኔታው ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

የእንስሳት ተዋጽኦ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርብ ቢኾንም ዛሬ እነዚህ ጉዳዮች በአለመረጋጋቱ ውስጥ ፈተና ላይ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ የዓለም ዲፕሎማሲ ስኬት – የብሪክስ!
Next articleኢትዮጵያ በ73ኛው የአፍሪካ አሕጉር የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው።