
ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ከተመሰረተ 14 ዓመታትን ያሰቆጠረው የብሪክስ ሀገራት ከሰሞኑ 15ኛዉን ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስፐርግ አካሂዷል።
በብራዚል ፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ድርጅት ብሪክስ “BRICS” በሚል የአምስቱን ሀገራት ጥምረት ነው ስያሜውን ያደረገው፡፡
ብሪክስ የሀገራቱ ጥምረት የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር መሰረት ያደረገ እንደኾነ ነው የሚነገርለት፡፡ ቡድኑ በየዓመቱ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎችም በፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የቅንጅት ዘርፍ ላይ የሚያተኩር እና የአባል ሀገራቱን የንግድ ዕድሎች፣ የኢኮኖሚ ስምምነቶች እንዲሁም ትብብሮች ዙሪያ ይመክራል።
ሰሞኑን ባካሄደው 15ኛው ጉባኤ ደግሞ በዋናነት ቡድኑን ቁጥር ከፍ በማድረግ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መክሯል ተብሏል፡፡ እናም ኢራንን፣ ሳውዲ አረቢያን ፣የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች፣ ግብፅ፣ አርጀንቲና እና ኢትዮጵያን አባል እንዲኾኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ በዚህም እ.አ.አ ከሚቀጥለው ጥር ወር 2024 ጀምሮ በመደበኛነት የቡድኑ አባል ሀገራት እንደሚኾኑ አስታውቋል።
የብሪክስ እውነታዎች፡-
👉 አምስቱ አባል ሀገራት ከዓለም አቀፍ አጠቃላይ ምርት (GDP) ውስጥ 30 በመቶውን ድርሻ የያዘ ነው፡፡
👉 ስብስቡ አንድ አራተኛውን የዓለም ኢኮኖሚ እና ከ40 በመቶ በላይ የዓለም ሕዝብ የያዘ ነው፡፡
👉 በ2022 የብሪክስ ንግድ 162 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
👉 ቡድኑ በ2015 እራሱ የሚያሥተዳድረው አዲሱን የልማት ባንክን (NDP)ን አቋቁሟል፡፡
👉 ባንኩ ለመሰረተ-ልማት እና ፕሮጀክቶች ብድርን ለአባል ሀገራት የሚያመቻች ነው።
👉 ቡድኑን ለመጠናከር የተለያዩ ሀገራት እንዲቀላቀሉ ፍላጎት አለው ፤ በዚህም 40 የሚኾኑ ሀገራት ፍላጎት እንዳሳዩ እና ከነዚህም 20 የሚኾኑት በመደበኛነት እንደጠየቁ ተመላክቷል።
👉 ቡድኑ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ለማስተዋወቅ እንዲሁም በሀገራቱ የውስጥ መገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም እንቅስቃሴ ጀምሯል።
ቡድኑ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ ፖለቲካ፣ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ችግሮችን የሚመክት የሌሎች አቻ ዓለም አቀፍ ተቋም መመሥረትን ግብ ያደረግ ሥለኾኑም ነው የሚነገርለት፡፡
በዋናነትም ቡድኑን የሚቀላቀሉ ሀገራት የሕዝብ ቁጥር፣ የነዳጅ ድርሻ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የGDP እድገታቸው እንደታየ ነው የተመላከተው።
ከአዲስ አባላት ጋር ተያይዞ ቡድኑ ትልቅ ግምት እየተሰጠው ነው፡፡ ብሪክስ በተለይም ኢራንን፣ ሳውዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች በአባልነት እንዲቀላቀሉ ጥሪ መቅረቡ ቡድኑ በነዳጅ ምርት ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው እንደሚያስችል አስተያየት እየተሰጠበት ነው።
በተለይም ብሪክስ የራሱን ምንዛሪ ይዞ የሚመጣ ከኾነ ያለውን የዶላር ሥርዓት እንደሚቀይር እየተገለጸ ይገኛል።በዚህም እ.አ.አ በ2050 አባል ሀገራቱ የዓለምን ኢኮኖሚ ይመራሉ የሚል አስተያየት በኢኮኖሚ ተንታኞች እየተሰጠ ነው፡፡
ብሪክስ አዲሱ ልማት ባንክ ለአባል ሀገራቱ ለመሰረተ ልማትና ዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ያለመ መኾኑ ፤ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ለብሪክስ ሀገራት ተጨማሪ ደኀንነት ዋስትና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ዓለም ባንክ እና አይ. ኤም.ኤፍ ያሉ ተቋማትን ለመተካት የብሪክስ ሀገራት እየሠሩ ስለመኾናቸው በስፋት እየተነሳ ነው፡፡ እንዲሁም ከብድር ክፍያ ጋር እየታገሉ ላሉ ሀገራት የብድር አማራጮችን የሚያስገኝ ነው ተብሎለታል።
በተለይም ከነዳጅ ጋር ተያይዞ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ይጠቀሙት የነበረውን የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ በብሪክስ እንዲዘወር እንደሚያደርግ ይታመናል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ዓለም አቀፍ ቡድን ጎራ መቀላቀሏ የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት የመመረጧ አንዱ ምክንያት የአፍሪካ ኀብረት መቀመጫ መኾኗ፣ ወደ አፍሪካ መግቢያ ዋነኛዋ በር የመኾኗ፤ አዳጊ ኢኮኖሚ ያላት መኾኑ፤ በአየር ንብረት መዛባት ላይ የምትሠራው ሥራ፤ ከገጠማት የሰሜን ጦርነት እና መውጫ መንገዶቿን የተመለከቱ ጥረቶች እና ሌሎችም ለብሪክስ አባልነት እንዳሳጫት ማሳያ ናቸው ተብሏል፡፡
በመኾኑም የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መቀላቀል ትልቅ የኢንቨስትመንት እና እድገት እድል የሚፈጥር መኾኑን እየተገለጸ ይገኛል።
ብሪክስ እንደ ሩሲያ እና ኢራን የምዕራቡ ማዕቀብ ላለባቸው እና እንደ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና አርጀንቲና የዶላር እጥረትና የዋጋ ግሽበት ላለባቸው ሀገራት ወሳኝ እንደኾነ ነው የሚነገረው፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መኾኗ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለመሻገር እድል የሚሰጥ ይኾናል፡፡ በቴክኖሎጂ፣ ትምህርት፣ ውትድርና፣ ሕክምና እና በመሳሰሉት ተጠቃሚ እንድትኾን ያስችላታል ተብሎለታል፡፡
በኢንቨስትመንት፣ ሥራ ፈጠራ እና ገቢን ለማሳደግ ያግዛል። ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነቷን ያሳድጋል፣ በውኃ ጉዳይ ከግብፅ ጋር በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ መኾናቸው ያለ አድሎ ሊስተናገዱ እና አለፍ ሲልም የሁለቱንም ሀገራት ጥቅም ያገናዘበ ድርድር እንዲያደርጉ እድል እንደሚሰጥም ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾኗን እንደስኬት የሚቀጥሩ አካላትም አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር፤ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አገሪቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ መስኮች ያስመዘገበችው ስኬት መገለጫ መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾኗ ለባለብዙ ወገንና ለሁለትዮሽ ግንኙነት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ጥረቷ ዕውቅና የሠጠ ነው ብለውታል አምባሳደር ጀማል በከር፡፡
ቡድኑ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች፣ ፍትሐዊና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የዓለም ሥርዓት እንዲፈጥር የበኩሏን ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያደርግ መኾኑንም ነው የጠቀሱት።
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!