በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የማዕድን ሃብትን ለማልማት የክልሉ ሰላም እንዲረጋጋ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡

50

ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት እና የሠላም እጦት በማዕድን ሃብት ልማት እንቅስቃሴው ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተጠቁሟል፡፡

ከአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ እንደተገኘው መረጃ በአማራ ክልል ከማዕድን ሃብት ልማቱ በዓመት ከ80 ሚሊየን በላይ ብር ገቢ ይሠበሰብ ነበር፡፡ ከውጭ ምንዛሬ አንጻርም ከ10 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ይገኝ ነበር፡፡ በዘርፉ ከ49 ሺህ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጠርም ታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይታየው ተስፋሁን ለአማኮ እንደገለጹት ማዕድን ሰላም ይፈልጋል፣ ሰላም ከሌለ ማዕድን ማምረት አይቻልም ብለዋል፡፡ ማዕድንን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብም ኾነ ለማምረት ሰላም አስፈላጊ ነው የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት እንቅፋት እየፈጠረ እንደኾነ ያነሳሉ፡፡

የተለያዩ የማዕድን አምራች ግብዓት ምርት የሚያገኙት ሩቅ ከኾኑ ወረዳዎች በመኾኑ በአግባቡ ግብዓት እየቀረበ አለመኾኑንም ያነሳሉ፡፡

አቶ ይታየው ክልሉ ላይ ችግር በተፈጠረባቸው ቀናት ውስጥ ከሰባት እስከ አስር ሚሊየን ብር በላይ ሊያጣ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገባው የማዕድን ሃብት እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ በሀገሪቱም ኾነ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ “የሰላም ዋጋው አይተመንም” የሚሉት አቶ ይታየው ትናንት በፈለግነው ሰዓት መረጃ በአግባቡ እንሰበስብበት የነበረው አግባብ መቋረጡ የመረጃ ቋታችን እንዲሳሳ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ከ49 ሺህ በላይ ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሮ የቆየው የማዕድን ልማት በሰላም እጦቱ ምክንያት ብዙዎችን ከሥራ ውጭ በማድረጉ የሠራተኞችን ሕይወት ፈትኗል፡፡

ከማዕድን ልማቱ በ10 ዓመት ውስጥ 100 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ያቀደው ቢሮው እያንዳንዷ ቀን ዋጋ እያስከፈለችው እና ከገቢ ውጭ እያደረገችው በመኾኑ እቅዱን ለመከለስ እንደሚገደድ አንስተዋል፡፡ ሰላሙን ለማስጠበቅ እና አካባቢው ተረጋግቶ ሁሉም ወደቀደመ ሥራው እንዲመለሥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ ይታየው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እየተሳተፉ ነው” የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ
Next articleየኢትዮጵያ የዓለም ዲፕሎማሲ ስኬት – የብሪክስ!