“በአማራ ክልል 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እየተሳተፉ ነው” የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ

52

ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡ ቢሮው ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራውን ያስጀመረው፡፡

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተሾመ ፈንታው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በግለሰብ፣ በተቋም እና በማኅበረሰብ ደረጃ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በማኅበረሰብ ደረጃ የመረዳዳት እና የመደገጋፍ እሴት እንዲዳብር ያደርጋል ብለዋል፡፡ የግለሰቦችን ግንኙነት እና ትስስርን እንደሚያጎለብትም ተናግረዋል፤ በተቋማት ደረጃም በጋራ የመሥራት ስሜት እንዲዳብር በማድረግ ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት 4 ነጥብ 87 ሚሊዮን ወጣቶች መመዝገባቸውንም አስታውሰዋል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከተመዘገቡት ወጣቶች መካከል 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከተመዘገቡት ወጣቶች መካከል 78 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ናቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተሳታፊ እየሆኑ ያሉት፡፡ ቢሮው በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሰራት ካቀደው አንጻር 73 በመቶ አፈጻጸም እንዳለውና ከተመዘገቡ ወጣቶች አኳያ ደግሞ 78 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አደረጃጀቶች እና ሌሎች መሣተፋቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በበጎ ፈቃድ የተሳተፉት የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች የኅብረተሰቡን ክፍተት መሙላታቸውንና የመንግሥትን የበጀት ጉድለት መሸፈናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአረጋውያንን ቤቶች የመገንባት፣ ነባሮችን የማደስ ሥራ የተሠራ ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ ቤቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መሠራታቸውን፤ከ2 ሺህ በላይ ነባር ቤቶችም መጠገናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ይተክላቸዋል ተብለው ከታቀዱ ችግኞች መካከል ሃምሳ በመቶውን በክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ለማስተከል አቅደው እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከ390 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በወጣቶች መተከላቸውንም ገልጸዋል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች የተተከሉ ችግኞች የእቅዳቸውን 46 በመቶ ማሳካታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ ሥራ እንደሚሰራ የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው 5 ሺህ 264 የሚደርሱ ወጣቶች ደም መለገሳቸውንም ገልጸዋል፡፡ በክረምት የበጎ ፈቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት መሥጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ለተማሪዎች የሚውሉ የቁሳቁስ ማሰባሰብ ሥራ አሁንም እተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊው በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ሥራዎችን ለመደገፍ እና ለማበረታት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውም አስታውቀዋል፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ባለው ቀሪ አንድ ወር የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራሮችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

አቶ ተሾመ አሁንም በክልሉ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡ አሁን ላይ ሰላምን የሚያመጡና የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በስፋት እንሰራለንም ብለዋል፡፡ በማጠቃለያ ሥራቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ ለነበራቸው አካላት ዕውቅና እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልጌሎት ሲጠናቀቅ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው እንደሚጀምርም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 6ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች።
Next articleበርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የማዕድን ሃብትን ለማልማት የክልሉ ሰላም እንዲረጋጋ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡