ጅግዳን ኮሌጅ በርቀት፣ በቀንና በማታ በተለያዮ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 319 ተማሪዎች አስመረቀ።

114

አዲስ አበባ: ነሐሴ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጅግዳን ኮሌጅ በ2006 ዓ.ም በህንድ ከሚገኝው ታሚናዱ ዮኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛው ዲግሪ ተማሪዎችን በማሰልጠን ነው ሥራውን የጀመረ።

ኮሌጁ በሀገሪቱ በሚገኙ 15 ቅርንጫፎች እስካሁን በተለያዮ የትምህርት መስኮች ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።

ኮሌጁ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ የምረቃ መርሐ ግብርም በርቀት፣ በቀን እና በማታ በመጀመሪያእና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዮ የትምህርት ክፍሎች ያሰለጠናቸውን 319 ሰልጣኞችን አስመርቋል።

ኮሌጁ በ2015 ዓ.ም በ15 ቅርንጫፎች 2812 ተማሪዎችን ማስመረቁንም የኮሌጁ ሥራ አስኪያጅ አቶ አማኑኤል መኮነን ገልጸዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም ኮሌጁ ተማሪዎችን ከማሰልጠን በተጨማሪ የተለያዮ የምርምር ሥራዎችን እንደሚሰራ ጠቅሰው በቀጣይም ኮሌጁ ተማሪዎችን በጥራት እና በብቃት አሰልጥኖ ለማስመረቅ የበለጠ እንደሚተጋ ተናግረዋል።

የኮሌጁ መስራች እና ባለቤት የሆኑት አቶ እውነቱ አበራ ባስተላለፉት መልዕክትም ተመራቂዎች በትምህርቱ ሂደት ያገኙትን ዕውቀት በመገምገም በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ በእውነት እና በመልካምነት ሕዝቡን ሊያገለግሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የትምህርት ጥራትን እና የሀገር እድገትን ስለሚጎዳ ሁሉም አጥብቆ ሊጸየፈው እንደሚገባ የኮሌጁ መስራች ተናግረዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የባሕር ዳር ዮኒቨርሲቲ የግዕዝ ትምህርት ክፍል ኅላፊ ዶክተር አባ በአማን ግሩም ማወቅ መመራመር የሚቆም ባለመሆኑ በየዕለቱ ለማወቅ እና ባወቅነው ልክም ሕዝቡን በመልካምነት ማገልገል ይገባል ብለዋል። ተመራቂዎቹ ያገኙትን ዕውቀት ማወቅ ለሚገባቸው እንዲያካፍሉ ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሌጁ በከፍተኛ ውጤት ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ሰልጣኞችም ሽልማት አበርክቷል።

ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አገኘች፡፡
Next articleተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ድርድር በዛሬው እለት በግብፅ ካይሮ ተጀመረ።