የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ፡፡

374

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 23/2012ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ነው፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን አጽድቋል፡፡

እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ሥርዓትን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እና ‹የሚናማታ› ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በተጨማሪም ዓይነ ስውራን፣ ለንባብ የዕይታ ችግር ላለባቸው እና በመደበኛ የንባብ ስልት ለማንበብ አካላዊ ችግር ላለባቸው ሰዎች የቀለም ጽሑፍ ሕትመት ሥራዎችን ተደራሽነትን ለማመቻቸት የወጣውን ‹የማራከሽ› ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በኳታር መንግሥት መካከል የተፈረመውን የኢንቨስትመንት ማስፋፋት እና ጥበቃ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እንዲሁም በአፍሪካ ሕዝቦች እና ሰዎች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ የማድረግ የአፍሪካ ኅብረት የካምፓላ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በመምራት ጉባዔውን አጠናቅቋል።

ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው

Previous article‹‹መንግሥት መረጃን ቀድሞ በማነፍነፍ ዜጎች ላይ ሊደርስ ከሚችለው አደጋ መታደግ አለበት፡፡›› አስተያየት ሰጪዎች
Next articleኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ባለፉት ሁለት ዓመታት 138 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኃይል ሽያጭ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡