“ሰው ሠራሽም ኾነ የተፈጥሮ አደጋዎች ቢከሰቱ መረጃ ማግኘትና ምላሽ መሥጠት እንዲቻል ለክልሉ ወደሰላም መመለስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባላል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

58

ባሕር ዳር: ነሐሴ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ የተፈጠረው አለመረጋጋት የኢንስቲትዩቱን የሥራ እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡

አቶ በላይ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አራት ዋና ዋና ዓላማዎችን ተግባራዊ በማድረግ ማኅበረሰቡን እያገለገለ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ ከተሠጡት ከተግባራቱ መካከል ፦

👉የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መከላከል እና መቆጣጠር በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች የሚከሰቱ አደጋዎች ቀድሞ መከላከል ፣መዘጋጀት፣ ምላሽ መሥጠት፣

👉በክልሉ የጤና ምርምር ማሳደግ በክልሉ የጤና ችግሮች

👉የላብራቶሪ አገልግሎት በሁሉም ማሳፋፋት ማጠናከር ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ፣ የሪፈራልን ማሳደግ፣ መረጃዎችን መተንተን

👉ጤና እና ጤና ነክ መረጃዎችን መቀመር መተንተን እና የመረጃ ማዕከል ኾኖ ማገልገል የሚሉት ናቸው ብለዋል፡፡

ተቋሙ እንደማንኛውም የክልሉ ተቋማት ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግ ማኅበረሰቡን ሲያገለግለ እንደቆየም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት እነዚህን ተግባራት በአግባቡ በማከናወን ማኅበረሰቡን ማገልገል አለመቻሉን ያነሳሉ፡፡

በተለያየ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት ሰው ሠራሽም ኾነ የተፈጥሮ አደጋዎች ቢከሰቱ የጤና ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊውን መረጃ ማግኘትም ምላሽ መሥጠትም እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

አቶ በላይ አሁን የክልሉ ሰላም እየተረጋጋ ቢሆንም ተንቀሳቅሶ ለመሥራት እና በየደረጃው ካሉ አካላት መረጃ ለማግኘት እንዳልቻሉ ይጠቅሳሉ፡፡

የጤና መረጃዎችን ከታች ከማኅበረሰቡ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ለመሰብሰብም እንዳልተቻለ ያነሳሉ፡፡

በተለይ መረጃዎችን ከጤና ኬላዎች፣ ከጤና ጣቢያዎች፣ ከሆስፒታሎች እና ሪፈራል ሆስፒታሎች ላይ ወደ ክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ይመጡ የነበሩ መረጃዎች በመቋረጣቸው ትንተና ማድረግ አለመቻሉን ያነሳሉ፡፡

በክልሉ ከ5ሺህ የማያንሱ የጤና ድርጅቶች አሉ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከእነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ መረጃዎች ክልሉ ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩ ቢኾንም አኹን ያለው ተጨባጭ ኹኔታ ይህን ለማድረግ አለማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡

መረጃዎች በክልሉ ታጥረው የሚቀሩ ሳይኾኑ ለፌዴራል እና ለዓለም የጤና ድርጅት የሚደርሱ በመኾናቸው ወደ ቀደመ ሰላማችን የምንመለስበት ኹኔታ እንዲኖረም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ የኢንተርኔት መቋረጥ የኅብረተሰብ ጤና ችግሮች ቢፈጠሩ መረጃውን ማድረስ እና ምላሽ መስጠት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በዚህ የተነሳ ክልሉ ድጋፍ እንዲያገኝ ለዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች ወደ ክልሉ ገብተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጋቸውንም አቶ በላይ አንስተዋል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካለት ተፈናቅለው በክልሉ እንደሚገኙ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ አካላት በየእለቱ የጤና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡

ካሁን በፊት ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ባሉበት አካባቢ የሚገኙ የቀን ሠራተኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግ መቆየቱን የሚያነሱት አቶ በላይ አሁን ይኽ አስቻይ ኹኔታ በተሟላ መልኩ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የመረጃ ቅብብሎሽ አለመኖር ለውሳኔ እንደሚያዳግት የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ መረጃ ለማግኘት ደግሞ ሰላም ቀዳሚው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲሶቹ መሪዎች የተቀበሉት ኃላፊነት የአማራ ሊሂቃንን እና የመላውን የአማራን ሕዝብ እገዛ የሚጠይቅ ነው” አቶ ደስታ ሌዳሞ
Next articleኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አገኘች፡፡