
ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር በዓለ ሲመት በባሕርዳር ተካሂዷል። በበዓለ ሲመቱ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለአዲሱ ርእሰ መሥተዳድር እንኳን ለታላቁ ኃላፊነት አበቃዎት ብለዋል። የቀድመው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ላደረጉት አበርክቶም አመሥግነዋል።
ኢትዮጵያ የሁላችን፤ ሕዝቦቿም የሁላችን ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ለጋራ ችግሮቻችን በጋራ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ጥያቄ ጥያቄያችን ነው፣ የጋራ ችግሮቻችንን በንግግር መፍታት ይገባናል ብለዋል። የአማራ ሕዝብ የብዙ ሺህ ዓመት የመንግሥት ታሪክ ያለው፣ መምራት የሚችል፣ ታጋሽ ፣ ችግሮችን የመፍታት ጥበብ ያለው፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለሀገሩ ቀናዒ፣ ለሀገር አንድነት ክብር ሕይወቱን የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በክልሉ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲቃጡ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ታላቅ ታሪክ ላለው ሕዝብ ችግሮቹን በብልሃትና በንግግር መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል። በአማራ ሕዝብ ላይ ከዚህ በፊት የደረሰው ችግር አሁን ላለው ችግሩ መንስኤ እንደኾነ እናምናለን፣ ነገር ግን ችግሮችን በስክነት መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
ከአማራ ሕዝብና መንግሥት ጎን በጋራ በመቆም ችግሮችን ለመፍታት ኃላፊነት ይዘን እንሄዳለንም ብለዋል።
አዲሶቹ መሪዎች የተቀበሉት ኃላፊነት የአማራን ሊሂቃንን፣ የሁሉንም ክልሎች እና የመላውን የአማራን ሕዝብ እገዛ የሚጠይቅ መኾኑንም አመላክተዋል።
የአማራ ሕዝብ መሪዎችን እንዲደግፍና አብሮ እንዲሠራ አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!