
የወንጀልን እንቅስቃሴን በተሻለ መልኩ ለመከላከል እንደተቋም የለውጥ ሥራ መሥራት ስለተጀመረ የተሻለ ለውጥ እንደሚኖር የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ::
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 23/2012ዓ.ም (አብመድ) የማኅበረሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ከላይ ያለውን የመንግሥት መዋቅር ብቻ ሳይሆን ከታች ያለው ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሠራበት እንደሚገባ የደሴ ከተማ ነዋሪ መምህር ይመር ሠኢድ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
መምህር ይመር ሠኢድ ‹‹ከታች ከጎጥ እና ከቀበሌ ጀምሮ ያለው የፀጥታ መዋቅር በደንብ መሥራት አለበት፤ ካልሆነ ጉዳዩን ወደ ዞን ብሎም ወደ ክልል ከወሰድነው ምንም ለውጥ አይመጣም›› ብለዋል፡፡
ይህን አሠራር ለማቀላጠፍ ከላይ ያለው የመንግሥት መዋቅርም ከታች ያለውን የመንግሥት መዋቅር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት መምህር ይመር አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ማንኛውም የወንጀል ወይም የሽብር ሥራ ከመፈጸሙ በፊት የደኅንነት እና መረጃን ቀድሞ የማግኘት ሥራን በመሥራት አስቀድሞ መከላከል ላይ መሥራት እንዳለበትም መክረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ዲበኩሉ መሠረት ‹‹መንግሥት ከማኅበረሰቡ ያገኘውን መረጃ ተጠቅሞ የሕዝቡን ደኅንነት የማይጠብቅ ከሆነ ‹ቀጥልበት› ማለቱ ነው፡፡ መረጃን ከመናቅ ይልቅ እንደ ሀብት በመጠቀም የወንጀል ድርጊትን ማክሸፍ መንግሥት ይጠበቅበታል›› ብለዋል፡፡
በየደረጃው ያለ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ግዴታውን የማይወጣ ከሆነ የእርማት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አቶ ዲበኩሉ አሳስበዋል፡፡
‹‹ጥቂት ግለሰቦች በሃይማኖት እና በብሔር ሰበብ የማኅበረሰቡን ደኅንነት እና እንቅስቃሴ ሲገቱ ይታያሉ፤ እነዚህ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሠላም የማይፈልጉ ስለሆነ ማንኛውንም የሕዝቡን ሠላም ከማወካቸው በፊት መረጃን በማግኘት ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል፡፡ ወንጀል ከተከሰተ ደግሞ ወንጀለኞችን በመለየት ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል›› ያሉት ደግሞ አቶ መንግሥት ከበደ ናቸው፡፡
በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጀማል መኮንን እንደተናሩት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ኅብረተሰቡን አስተባብሮ፣ ኅብረተሰቡ እና ፖሊስ በጋራ በመሆን ወንጀልን ቀድመው በመከላከል በኩል ተጨባጭ የሆነ ሥራ ሲሠሩ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ድጋፍ እና ክትትል እየቀነስ ሲመጣ ይህ አሠራር እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ከማኅበረሰቡ ከሚገኘው ጥቆማ በተጨማሪ ፖሊስም በራሱ አሠራር ጥናት አድርጎ ወንጀል ሊከሰት ይችላል ብሎ የጠረጠረበትን አካባቢ ኅብረተሰቡን የማንቃት፣ የማስገንዘብ እና የፀጥታ ኃይሎችን አደራጅቶ የመሥራት ሥራ ይጠበቅበታል›› ብለዋል፡፡
የወንጀልን እንቅስቃሴን በተሻለ መልኩ ለመከላከል እንደተቋም የለውጥ ሥራ መሥራት እንደተጀመረ የተናገሩት ኮማንደር ጀማል ‹‹ከኅዳር 10 ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙትን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአዲስ መልኩ መመደብ ተጀምሯል፡፡ ይህን ማድረግ ያስፈለገው ቀደም ሲል የተስተዋለውን የመፋዘዝ ሁኔታ የማንቃት፣ የሞራል፣ የተሻለ የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ያለው እንዲሁም በማኅበረሰቡ ቅቡል የሆኑ ኃላፊዎችን በመምረጥ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ነው›› ብለዋል፡፡
ይህን ለማሳካት የሰው ኃይል የማሟላት እና ስልጠና የመስጠት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኮማንደሩ አሳስበዋል፡፡ ተቋሙ በፊት ተቀዛቅዞ የነበረውን አሠራር ለማንቃት እና ለማዘመን አሁን አዲስ ሥር ነቀል አሠራር ይዞ ስለመጣ ኅብረተሰቡ በግባትም ሆነ መረጃን በማቀበል የነበረውን ተሳትፎ በማሳደግ ከጎናቸው እንዲቆምም ኮማንደር ጀማል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ