ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠ ወቅታዊ መረጃ

282

ቁጥር – አራት

የአማራ ክልል ጽንፈኛ እና ዘራፊ ቡድኖች ከደቀኑበት የዝርፊያ፣ የወድመትና የመፍረስ አደጋ በመውጣት ወደ ቀደመዉ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሰ ይገኛል። በክልሉ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ በባሕር ዳር ከተማ ተደርጓል። በክልሉ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታ መስተዳድርም እንደገና ተደራጅቷል፡፡

ለዚህ አስቸኳይና ታሪካዊ ጉባኤ መሳካት ድጋፍ ያደረጋችሁ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙና የአራቱ ቀጠና ኮማንድ ፖስት አመራሮች፣ የክልሉ መንግሥት መዋቅር፣ ሰላም ወዳድ የክልሉ ሕዝቦች እና የተከበራችሁ የክልል ምክር ቤት አባላት ምስጋና ይገባችኋል። ይህ ጉባኤ እንዳይሳካ ከውጭና ከውስጥ የነበረውን ሤራ የምክር ቤት አባላቱ በቆራጥነት አልፈውታል። ምክር ቤቱ በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከመከረ በኋላ ችግሩን ከሥረ መሠረቱ ለመፍታት የክልሉ መስተዳድር እንደገና እንዲደራጅ ወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት አዲስ ርዕሰ መስተደድርና የካቢኔ አባላትን ሾሟል፡፡

ክልሉ በጽንፈኞችና ዘራፊዎች ከተደቀነበት አደጋ ወጥቶ ወደ መደበኛ ሁኔታ በመመለስ ለዚህ በመብቃቱ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ታላቅ ደስታ ተሰምቶታል፡፡ ይህም ስኬት የክልሉ ሕዝብ ችግሮችን በኃይልና በሕገ ወጥ መንገድ ሳይሆን በዉይይት፣ በድርድርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለዉን ቁርጠኛ አቋም ያረጋገጠ ነዉ፡፡

አዲሱ የክልሉ አመራር የወደፊት የሥራ ዘመኑ የሰላም፣ የልማት፣ የስኬትና የብልጽግና እንዲሆንለት እየተመኘን፣ በቀጣይ ለሚያደረገዉ እንቅስቃሴ የዕዙ የቅርብ ድጋፍ እንደማይለየው ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የጀመረዉን ሕግ የማስከበር ሥራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለአዲሱ አመራር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያደርገዉን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ

Previous articleበየደረጃው ያሉ መሪዎች ለሕዝብ ጥቅም እንዲሠሩና ሕዝብን እንዲያሻግሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ።
Next article“የአማራ ክልል ድል ድላችን ነው ፤ ፈተናውም ፈተናችን ነው” አቶ ሽመልስ አብዲሳ