በየደረጃው ያሉ መሪዎች ለሕዝብ ጥቅም እንዲሠሩና ሕዝብን እንዲያሻግሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ።

105

ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር በዓለ ሲመት ተካሂዷል። ለቀድሞው ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እና ካቢኒያቸውም አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። በበዓለ ሲመቱ ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በበዓለ ሲመታቸው ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪውን ተቀብለው ለመጡ እንግዶች ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። የአማራ ሕዝብ ለሀገር ግንባታ ያለውን አስተዋጽኦ ተረድታችሁና አሁን ላይ ያለውን ችግር አውቃችሁ በመምጣታችሁ ክብር ይገባችኋል ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር በተለይም ለአማራ ክልል ሕዝብ እያደረገው ላለው አስተዋጽኦ እና ተጋድሎ ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል። ሕዝብን ከአደጋ ለማላቀቅ የውስጥ ችግራችንን መፍታት ይገባናል ብለዋል።

አጣቃሽና እንደየኹኔታው የምንቀያየር ፖለቲከኞች በመኾናችን ችግሮችን መፍታት አልቻልንም ነው ያሉት። ገቢራዊ ሥራ ባለመሥራታችን ችግር ውስጥ ቆይተናልም ብለዋል። የክልላችንን ችግሮች በተደጋጋሚ ተነጋግረንባቸዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በተግባር ችግሮችን ካልፈታን ሕዝባችንን ለአደጋ እናጋልጣለን ብለዋል። በቁርጠኝነት ለምናደርገው እንቅስቃሴ ሁላችሁም ከጎናችን እንድትኾኑ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ ተገኝታለች ፤ ኢትዮጵያን ይዘን በጋራ እንሠራለን ብለዋል። በፓርቲው የጋራ ዓላማና ጥቅም በመነሳት በጋራ መሥራት ይገባል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ። ከዚያ ውጭ ያለው አካሄድ አዋጭ አለመኾኑንም አመላክተዋል። ከዚህ በኋላ ችግር የሚያስተናግድ አቅም የለንም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሮቻችንን ካልፈታን ሀገርና ሕዝብ አደጋ ላይ እንጥላለን ብለዋል።

ከታሪክ ተወቃሽነት ለመውጣት በጋራ መሥራት ይገባናልም ሲሉ አሳስበዋል። በየደረጃው ያሉ መሪዎች ለሕዝብ ጥቅም እንዲሠሩና ሕዝብን እንዲያሻግሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Hagayya 15/2015
Next articleከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠ ወቅታዊ መረጃ