ከ7 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መገኘቱን የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

578

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 23/2012ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አብጠራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ዲያቆን ባይለየኝ አሰማ በንብ ማነብ ሥራ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ዲያቆን ባይለየኝ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት 110 ቀፎ ንብ አላቸው፤ 75 በዘመናዊ ቀፎና ቀሪዎቹ በሽግግርና በባህላዊ ቀፎ ናቸው፡፡ ከአንዱ ዘመናዊ ቀፎ እስከ 40 ኪሎ ግራም ማር ያገኛሉ፡፡ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ አንዱን ኪሎ ግራም በሁለት መቶ ብር በመሸጥ ገቢ እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዲያቆን ባይለየኝ ሙሉ መተዳደሪያቸው ከማር ምርት የሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ በዚህ ሥራቸው ደስተኛ ናቸው፡፡ ዘመናዊ ቀፎ፣ የማር ማጣሪያና መሰል የዘርፉ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በቀጣይ ማር የማሸግ እና የማከፋፈል እቅድም አላቸው፡፡

ለንብ ማነብ የግብርናው ዘርፍ ተስማሚ ከሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የአማራ ክልል አንዱ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም የወጣው የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው ክልሉ በባህላዊ፣ በሽግግርና በዘመናዊ ቀፎዎች 1 ሚሊዮን 154 ሺህ 94 የንብ መንጋ አለው፡፡ በዚህ ሀብቱም የሀገሪቱን 18 በመቶ ይሸፍናል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር ዞኖች በቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የንብ መንጋ ያላቸው አካባቢዎች መሆናቸውን መረጃው ያሳያል፡፡

የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የንብና የሀር ልማት ባለሙያ አቶ ሙሐመድ ጌታሁን በሰጡት ማብራሪያ እስካሁን 7 ሺህ 825 ቶን የማር ምርት ተገኝቷል፡፡ 24 ሺህ ቶን የማር ምርት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ይገኛል ተብሎ ታልሞ እየተሠራም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የክረምቱ ዝናብ እስከ ጥቅምት መቆየቱ የንቦች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ የወቅቱን የማር ምርት እንዲቀንስ አድርጎታል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የተጠቃሚዎች ፍላጎት መጨመር ለወቅቱ የማር ዋጋ መናር እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል ባለሙያው፡፡

የአማራ ክልል ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ አምራቾች የሚያመርቱትን የማር ምርት ለገበያ ያቀርቡ ዘንድ የገበያ ትስስር እየፈጠረ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡ የቢሮው የማር፣ የወተትና የእንስሳት መኖ ግብይት ባለሙያ አቶ የኔ ገዳም ተስፋ እንዳስታወቁት በኅዳር ወር ብቻ 2 ሺህ 106 ቶን ማር ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 500 ሺህ ቶን ማር እንደሚመረት ከሪፖርተር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ ከሚመረተው የማር ምርት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ለጠጅ መጣያነት አልያም ለቤት ውስጥ ፍጆታ ብቻ እንደሚውል መረጃው አመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleአቶ ወርቁ አይተነው ቃል የገቡትን የአምስት ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጋቸውን የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡
Next article‹‹መንግሥት መረጃን ቀድሞ በማነፍነፍ ዜጎች ላይ ሊደርስ ከሚችለው አደጋ መታደግ አለበት፡፡›› አስተያየት ሰጪዎች