“የዜጎችን መብትና ጥቅም አስከብረን፣ ሀገራችን የበለጠ የከፍታ ምዕራፍ እንድትወጣ መሥራት አለብን” የቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

103

ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እና ካብኒያቸው አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ባለቤት ናት፣ በረጅም ታሪኳ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች ነው ያሉት። የእኛ እጣ ፋንታ በአብሮነት እንጂ በመነጣጠል አይደለም ብለዋል። የጋራ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል፡፡ ችግሮችን መፍታት ያለብን በአንድነት ነው፣ ዕጣ ፋንታችን አንድና አንድ መኾን ብቻ ነው ብለዋል።

የዜጎችን መብትና ጥቅም አስከብረን፣ ሀገራችን የበለጠ የከፍታ ምዕራፍ እንድትወጣ መሥራት አለብን ነው ያሉት። በሥራ ጊዜአቸው ከክልሎች ጋር በመነጋገር በርካታ ችግሮችን መፍታታቸውን የተናገሩት ዶክተር ይልቃል ብዙዎቹ በተፈቱበትና ባመጡት ለውጥ አግባብ አልተነገሩም ብለዋል። የተፈቱት ችግሮች ባለመነገራቸው ሕዝቡ መንግሥትን እንደማይፈታ አስቆጥሮታል፣ ይሄም ችግር ፈጥሯል፣ ይሄ ወደፊት መስተካከል ይገባዋል ነው ያሉት።

ችግር ሁል ጊዜ ይኖራል፣ ትልቁ ነገር ችግርን መፍታትና እንዳደገም ማድረግ ነውም ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ችግር የሚፈታው በመላው ኢትዮጵያ ትብብር መሆኑንም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ ችግር የጋራ ችግር ነው እያሉ የሌሎች ክልሎች መሪዎች አጋርነታቸውን እያሳዩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ሕዝባችን መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉበት ያሉት ዶክተር ይልቃል አንዳንዶቹ ጊዜ የሚጠይቁ፣ ውይይት የሚያስፈልጋቸው፣ የሌሎችን እገዛ የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።

በኃይል ችግርን መፍታት በፍጹም አዋጭ አለመኾኑንም አንስተዋል። እቆረቆርለታለሁ የሚሉትን ሕዝብ ሰላም እያሳጡ ችግርህን እፈታልሃለሁ ማለት አይገባም ነው ያሉት። ፖለቲካችን በስክንነት ካልተመራ በስተቀር እርስ በእርስ ተጠፋፍተን እናልቃለን እንጂ የምናሳካው አንድም ዓላማ የለም ብለዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ችግሮችን ለመፍታት አመራሩን በማገዝ መሥራት እንደሚገባውም ገልጸዋል።

ለእኔና ለጓደኞቼ የተሰጠን ክብር ትልቅ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል ሕልማችን የአማራ ሕዝብ ሰላምና ልማት ነውም ብለዋል። በቀጣይም ለክልሉ ሕዝብ ሰላምና ልማት እንሠራለን ነው ያሉት። የአማራ ክልልን መንግሥት በማፍረስ የሚመለስ ችግር አለመኖሩንም አመላክተዋል። መሪን በመግደልና በማንቋሸሽ ችግር አይፋታም ያሉት ዶክተር ይልቃል መላው ሕዝብ ተተኪ መሪዎችን እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞው ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ለአዲሱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ስልጣናቸውን አስረክበዋል። ለተደረገላቸው ሁሉ አመስግነዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያለ አግባብ ትንኮሳዎችን እና የፖለቲካ ሥራዎችን በግልፅ በመታገል ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ እንድናጸና አደራ እላለሁ” አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Hagayya 15/2015