
ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት እየተካሄደ ነው። በበዓለ ሲመቱ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ምሥጋና አቅርበዋል።
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመሆን ሀገር የገነባ፣ ከሁሉም ጋር የተዋለደና የተጋመደ፣ ፍትሕን የሚሻና ለማግኘት የሚተጋ፣ ሀገር ወዳድ ታታሪና አቃፊ ሕዝብ ነው ብለዋል በመልእክታቸው። ባለፉት ዓመታት የተዘራው ሀሰተኛ ትርክት ለአገዛዝ እንዲመች ታስቦ እንጂ የአማራን ሕዝብ የሚገልጽ አይደለም፤ በተዘራው የሀሰት ዘር በማንነቱ ምክንያት ገፈት ቀማሽ ሆኖ ቆይቷልም ብለዋል። ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች በመመለስ ሕዝቡን እንድንክስ እጠይቃለሁ ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት የአማራን ሕዝብ የማይወክል ሕዝቡን ያበሳቆለ መሆኑንም ገልፀዋል። የሰላም እጦቱ ሕዝቡን እፎይ ብሎ ወደ ሥራ እንዳይገባ እንዳደረገውም ተናግረዋል። ሕዝቡ የሰጠንን ኃላፊነት በመወጣት ሰላምን ማረጋገጥ ትንሹ ኃላፊነት ነውም ብለዋል። ያለ አግባብ ትንኮሳዎችን እና የፖለቲካ ሥራዎችን በግልፅ በመታገል ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ እንድናጸና አደራ እላለሁም ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ውለታን የማይዘነጋ ፅኑ ሕዝብ መሆኑንም ገልፀዋል። የአማራ ሕዝብ ለእውነት ግንባሩ የማይታጠፍ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ሕዝቡን ካስተባበርነው ከገጠመን ችግር በቀላሉ መውጣት ይቻላል ነው ያሉት። አሁን ላይ ከፍተኛ የሀገር ኃላፊነት የምንሰጥበት ጊዜ ነውም ብለዋል።
“አዲስ የተሾሙትን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንድናግዝ አደራ እላለሁ” ብለዋል። የክልሉ ሕዝብም አዲስ ለተሾሙት መሪዎች በሙሉ ልብ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!