የደብረ ብርሀን ከተማ መምሪያ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን ገለጸ።

49

ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሀን ከተማ ለ2016 የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። በከተማው የመማር ማስተማሩን ሥራ በወቅቱ ለማስጀመር ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ተካሂዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥበቡ ገሰሱ በወቅቱ እንደገለጹት የ2016 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ የተሳካ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው። በአዲሱ የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛ፣ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ55 ሺህ በላይ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቶች ሳቢና ማራኪ እንዲሁም ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ እንዲሆኑ ሥራዎች መከናወናቸውንም አስታውቀዋል። በትምህርት ቤቶች በ10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የ20 አዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና የ45 ነባር የመማሪያ ክፍሎች የጥገና ሥራ መከናወኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ለውበትና ለጥላ የሚሆኑ የዛፍ ችግኞች መተከላቸውንም አመልክተዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በከተማው ድጋፍ ለሚሹ 6 ሺህ 200 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሆነው ተሾሙ፡፡
Next articleየቡዳፔስት ሌላ ክስተት!