
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡ ጉባዔው በጥዋት ሲጀመር ከተያዙት አጀንዳዎች መካከል አንዱ የተለያዩ ሹመቶችን መስጠት ነበር፡፡ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ልቃል ከፋለ ኅላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ሲመክር የዋለው ጉባዔው ከሰዓት እስከ እረፍት በነበረው ውይይቱ የማጠቃለያ ሃሳች ቀርበውበታል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ላለፉት 23 ወራት ክልሉን በርእሰ መሥተዳደርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ዶክተር ይልቃል ከፋለ የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ወደ ኅላፊነት የመጣንበት ወቅት ጦርነት የወለደው ውስብስብ የፖለቲካ ድባብ የሰፈነበት ወቅት ነበር ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል የተቃጣብንን ወረራ በድል ቋጭተን በርካታ የልማት ሥራዎችን አከናውነናል ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ውስብስብ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ወጥ ዓላማ፣ የጋራ ራዕይ፣ በቂ የትግል ስልት እና የሌሎችን አሰላለፍ ያልተረዳ በመሆኑ ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ተለይተው ያደሩት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ኾኖ ሳለ ዋልታረገጥ እሳቤዎች አብሮ ለመቆም የሚያስችለውን መድረክ ጠባብ አድርገውታል ነው ያሉት፡፡ በመሆኑም የክልሉን ሕዝብ ለዘመናት ከዘለቀው ማሕበረሰባዊ ወከባ ለማውጣት ስክነት፣ ስሌት፣ ብስለት እና ጥበብ በእጅጉ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ጦርነት በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጠረው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ሥብራት ገና በወጉ ሳያጠግግ እና ሳያገግም ክልሉን ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያመራ ማድረግ ለአማራ ሕዝብ ማሰብ ሳይሆን በአማራ ሕዝብ መነገድ መሆኑ ሊታዎቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ያልተገራ የብዙሃን መገናኛ ተቋማትን በመጠቀም ያልተገባ ሥም እና ዝና መስጠት ዘመን ያለፈበት የፖለቲካ አሰላለፍ በመሆኑ ሕዝቡ ሊገነዘብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ቱሪዝም እና ማእድን ዘርፍ የላቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለሥርዓት አልበኝነት መስፋፋት ምክንያት ነው ሆኗል ብለዋል፡፡ አሁናዊው የክልሉ ነባራዊ ሃቅ በከፋ ግጭት ውስጥ መሆኑ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ በምክር ቤቱ የተነሱት ነጥቦች ናቸው ብለዋል፡፡
ከማንነት እና ወሰን ጋር በተያያዘ ከማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በላይ የክልሉ መንግሥት ኮሚቴ አቋቁሞ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ጥያቄዎቹ በክልሉ ብቻ የሚፈታ አይደለም ብለዋል፡፡ የፌደራል ተቋማት ጥናት፣ የሌሎች አካላትን ይሁንታ እና በቂ ዝግጅት ያስፈልገው እንደነበር አንስተዋል፡፡ መንግሥታቸውም በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን መስራቱን አንስተዋል፡፡
አሁናዊ የክልሉ ትርምስም የክልሉ ሕዝብ ጥያቄ እንዳይመለስ የሚፈልጉ ኃይሎች እንደማይዘውሩት ምን ያክል እርግጠኞች ናችሁ ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ከግጭት በፊት ክልሉ ያሉበትን ጉዳዮች ማጤን ይገባ ነበር ነው ያሉት፡፡ ክልሉ በእጁ የገቡ መልካም አጋጣሚዎችን ማጽናት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ያሉት ዶክተር ይልቃል በሥልጣን ዘመናቸው የነበረውን አመራር “እዳ ከፋይ ነበር” ብለዋል፡፡
ትናንት የክልሉን ነባር ርስቶች ፈርመው እና ተስማምተው የሰጡ ሰዎች ዛሬ ላይ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ አቀንቃኝ ሆነው መመልከት አሳዛኝ ነበርም ብለውታል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡ አሁንም የተጀመሩ ሥራዎችን ማስቀጠል እና ለፍጻሜ ማብቃት የአማራ ሕዝብን የጋራ ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ወዳጅ እና ጥላትን የለየ በሳል የፖለቲካ ትግል እና ወዳጅ ማፍራት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መመሥረት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ከመንግሥት ውጭ የታጠቀ ኃይል መኖር መጨረሻው እንደ የመን እና ሱማሌ መሆን ነው ያሉት ርእስ መስተዳደሩ ከሌሎች መማር ካልቻልን ከማን ልንማር እንችላለን ነው ያሉት፡፡ ሕዝብን የሚያስከፉ በርካታ ችግሮች መኖራቸው እንደማይካድ አንስተው ካልሰራ አመራሩ ይወርዳል ፓርቲውም በምርጫ ይቀጣል እንጂ ኃይል በፍጹም አማራጭ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥት መወቀስ ካለበትም ሰላምን ለማምጣት ሰፊ ውይይት ያስፈልጋል ብለው ጊዜ መውሰዳቸው ብቻ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ከምንም በላይ መንግሥታዊ ሥርዓት መቅደም እንዳለበት ያነሱት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል በምክር ቤቱ የተወሰነውን የሠላም ሞሽን በመተግበር ላይ እያን ጥረታችን መከነ ብለዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲወሰን ጥሪ ያቀረቡትም ግጭቱ በጥቂት ቀናት ብቻ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን ተከትሎ ነበር ብለዋል፡፡
ሕዝብ እና መንግሥት የሰጠኝን ኅላፊነት በገባኝ እና በምችለው ልክ ተወጥቻለሁ ብየ አስባለሁ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ላለፉት ሁለት ዓመታት ማኅበራዊ፣ ቤተሰባዊ እና የጤና ችግሮቻቸውን ተቋቁመው ማገልገላቸውን አንስተዋል፡፡ ምንም እንኳን ለፖርቲያቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ካስገቡ ከስምንት ወራት በላይ ቢሆንም ወቅታዊ ሁኔታው እንዲቆዩ እንዳስገደዳቸው ጠቁመዋል፡፡ “በቀውስ ወቅት ወደ ሥልጣን መጥቶ በቀውስ ወቅት ኅላፊነትን መልቀቅ ህመሙን የማውቀው እኔ ብሆንም የምንችለውን ሁሉ ግን ሰጥቻለሁ” ፤ ጥያቄየንም ፓርቲየ ተቀብሎኛል ነው ያሉት፡፡
ምክር ቤቱም የርእሰ መሥተዳደሩን ጥያቄ ተቀብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!