
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ከሰዓት በኋላ ሲቀጥል በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ የሰጡት የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ እንዲሁም የኮማንድፖስቱ አባል አቶ ደሳለኝ ጣሰው በክልሉ ውስጥ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ከእውነት እና ከብስለት መመልከት ይገባል ብለዋል፡፡ የግል ፍላጎትን እና ምኞትን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ግን ብዙ የማያስኬድ ብቻ ሳይሆን የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍል አንስተዋል፡፡
የሰላም አማራጮችን እንደ መፍትሄ ለመውሰድ ባለፈው ጉባዔ ላይ ተወስኖ እንደነበር ያነሱት አቶ ደሳለኝ በየአካባቢው የተላኩ የምክር ቤት ልዑካን ሳይመለሱ ግጭት መፈጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡ አሁንም የሰላም አማራጮች ሙሉ በሙሉ ዝግ አይደሉም ነው ያሉት፡፡
የአማራ ሕዝብ ከለውጥ የተገፋ በማስመሰል የሚደረግ የኃይል አሰላለፍ ትክክል አለመሆኑን ያነሱት አቶ ደሳለኝ “የአማራ ሕዝብ ለውጡን በደሙ እና በድካሙ ያመጣ ሕዝብ ነው” ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ስጋት ማቃለል እንደቻለም ገልጸዋል።
ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቆየቱ ግን ዘርፈ ብዙ ችግር ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡ አዋጁ እንዲራዘምም ሆነ እንዲያጥር የሚያስችለው አቅም ያለው በክልሉ ሕዝብ መዳፍ ውስጥ በመሆኑ በትብብር እና በቅንነት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!