“የአማራ ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለው ክብር እና ፍቅር በተግባር ተፈትኖ የታየ በመኾኑ ወቅታዊውን ችግር በጋራ መፍታት ይገባል” የምክር ቤት አባላት

27

ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባዔውን በክልሉ ርእሰ መዲና ባሕር ዳር ከጠዋት ጀምሮ እያካሄደ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በ6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔው የክልሉን ወቅታዊ የፀጥታ ኹኔታ የጉባዔው ማዕከል አድርጎ እየመከረ ነው፡፡

የክልሉን ወቅታዊ የፀጥታ ችግሮች፣ አሁናዊ አስቻይና ፈታኝ ጉዳዮች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለውይይት መነሻ እንዲኾን ያነሱት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ እና የኮማንድፖስቱ አባል አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው፡፡ አቶ ደሳለኝ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ ሕዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር አንስተዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ ለውይይት ባቀረቡት መነሻ ሃሳብ ላይ የክልሉን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ፣ ኀይል የማያሰባስብ እና ወንድማማችነትን የሚጎዳ ካሉት የግጭት አዙሪት ለመውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ወደ አካባቢው የገባው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሰላም በሮች ዝግ አይደሉም ያሉት የኮማንድፖስቱ አባል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፍጥነት ለመውጣት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡

ከውይይቱ መነሻ ሃሳብ በኋላ ጥያቄ፣ የመፍትሔ መንገድ እና አማራጭ እይታ ያሏቸውን ሃሳቦች ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እንዲፈጠር የተደረገው ግጭት የሴራዎች ሁሉ ቁንጮ ነበር ብለዋል፡፡

ባለፈው ሥርዓተ መንግሥት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት አባልነት እራሱን እንዲያገል ብዙ እኩይ ተግባራት መሠራታቸው ሳያንስ አሁንም ከሠራዊቱ ጋር ግጭት ውስጥ እንድንገባ መደረጉ ተገቢ አይደለም ነው ያሉት፡፡

“የአማራ ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለው ክብር እና ፍቅር በጽንሰ ሃሳብ ሳይኾን በተግባር ተፈትኖ የታየ በመኾኑ ወቅታዊውን ችግርን በጋራ መፍታት ይገባል” ብለዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም ሕዝቡ ለሠራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር እያስመሰከረ መኾኑን የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡

ክልሉ ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች ብቻ ሳይኾን ቅሬታዎችም እንዳሉት በተደጋጋሚ አንስቷል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት አስፈጻሚው አካል እራሱን በደንብ እንዲፈትሽ ከአባላቱ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ቢያንስ በክልሉ አቅም መፈታት ያለባቸው የሕዝብ ጥያቄዎች በአፋጣኝ መመለስ እንዳለባቸውም ተነስቷል፡፡

ከሰላም ውጭ ያሉ የኀይል አማራጮችን እንደ መፍትሔ የማያስቀድም ትውልድ ለመፍጠር አመራሩ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

የኃይል አማራጭ ሰላም አያመጣም ያሉት አባላቱ ችግሩ ከአፈ-መዝ ወደ ጠረንጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲመጣም ጠይቀዋል፡፡

ክልሉን መሪ አልባ ለማድረግ፣ በሌሎች ወንድም ሕዝቦች የተሳሳተ እይታ እንዲኖረው እና ከምንም በላይ ጥያቄዎቹ እንዳይመለሱ የሚያደርጉ አካሄዶችን በአንክሮ ማሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሳለች” የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“የአማራ ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለው ክብር እና ፍቅር በተግባር ተፈትኖ የታየ በመኾኑ ወቅታዊውን ችግር በጋራ መፍታት ይገባል” የምክር ቤት አባላት