“ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሳለች” የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች

40

ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ችግሮች በከተማው ነዋሪ በተለይም ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ማስከተሉን በከተማዋ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጭዎች ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎች እንዳሉት ለሁለት ሳምንታት በቆየው የሰላም መደፍረስ የተሸከርካሪ እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ አቁመው ቆይተዋል፡፡

በዚሕም በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል ፤ በተለይም ደግሞ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ሕጻናት ተጠቂ መኾናቸውን ነው የገለጹልን፡፡

የታመሙ ሰዎችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ መቸገራቸውንም ነግረውናል፡፡

ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከሸቀጣሸቀጥ ላይ ዋጋ በመጨመር ማኅበረሰቡ የከፋ ችግር ላይ እንዲወድቅ ተደርጓል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ፡፡

ይሁን እንጂ ከተማው አሁን ላይ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሱን አንስተዋል፡፡

ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

መንግሥትም በቀጣይ በማኅረሰቡ የሚነሱ ጣያቄዎችን ተቀብሎ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ ከሁለት ሳምንታት በላይ የጸጥታ ችግር አጋጥሞ ቆይቷል፡፡

በዚሕም በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት፣ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች ሳይቀር ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹት፡፡

ይሁን እንጂ ከነዋሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት አሁን ላይ ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷን አንስተዋል። አገልግሎት መስጫ ተቋማትም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ፤ የትራንስፖረት ዘርፉም ሥራ ጀምሯል ብለዋል፡፡

የራስን ሃብትና ቅርስ በማውደም የሚፈታ ችግር እንደማይኖር የገለጹት ከንቲባው የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትምህርት ዘመኑን በሥኬት ለማጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራው መሠራቱን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“የአማራ ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለው ክብር እና ፍቅር በተግባር ተፈትኖ የታየ በመኾኑ ወቅታዊውን ችግር በጋራ መፍታት ይገባል” የምክር ቤት አባላት