
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የ2016 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ከከተማ አሥተዳደሩ የትምህርት ዘርፍ መሪዎች ጋር መክሯል።
በምክከሩ ላይ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባዬ አለባቸውን ጨምሮ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤት መሪዎች ተሳትፈዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ከነሐሴ 23 እስከ ጳጉሜ/2015 ዓ.ም ድረስ ተማሪ የመመዝገብ ሥራ እንደሚያካሂድም አሳውቋል።
የትምህርት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የትምህርት አመራሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባዬ አለባቸው ተናግረዋል።
አቶ ባዬ የ2015 ዓ.ም ከላይ እስከ ታች ያሉት መሪዎች በመናበብ በመሠራቱ ውጤት የተመዘገበበት ዓመት መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ለ2015 ዓ.ም አፈጻጸም መገምገሙ የ2016 ዓ.ም ሥራን በውጤት ለመምራት እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡
ባሕር ዳር የክልሉ መቀመጫ ከተማ ከመኾኗ ጋር ተያይዞ እሷነቷን የማይመጥኑ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መማሪያ ክፍሎችን የመገንባት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የ2016 ዓ.ም የትምህርት ሥራን በውጤት ለማጠናቀቅ የንቅናቄ ሥራው መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኀይለማርያም እሸቴ የትምህርት ዘመኑን በሥኬት ለማጠናቀቅ የክረምት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ውጤቱን ለማሳመር ቅድመ ዝግጅቱ ማማር አለበት የሚሉት ኀላፊው ቅድመ ዝግጅቱ በአግባቡና በወቅቱ መጠናቀቁን ያነሳሉ፡፡
የትምህርት መሪዎች ከትምህርት ቤታቸው አልተለዩም የሚሉት አቶ ኃይለማርያም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ባለሃብቶችን በማሳተፍ የመማሪያ ክፍሎችን የመገንባቱ ሥራ በሥፋት መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ትምህርት ቤቶች የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ለማድረግ በተሠራ ሥራ ከአንድ ትምህርት ቤት በስተቀር ሁሉም የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ ሕትመቱ መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡ በ2015 ዓ.ም ከነበረው አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል፡፡
የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙጨ ባዘዘው ትምህርት ቤቱ ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቆ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እየተጠባበቀ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ሥራው በቅደም ተከተል የሚሠራ መኾኑን የጠቆሙት ርእሰ መምህሩ ተማሪዎችን መመዝገብ እና መመደብ ቅድሚያ የሚሠጠው ሥራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
መምህራን በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ወደ ክፍል ገብተው መማር ማስተማሩ እንዲጀመር ወላጆች በተቀመጠው ቀነ ገደብ ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ከፋሲሎ ሁለተኛ ደረጃ የጉድኝት ማዕከል ጉድኝት አስተባባሪ ትበይን ባንቲሁን በጉድኝቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ቅድመ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቢሮ በሚሠጠው አቅጣጫ መሠረት ወደ ሥራ እንደሚገቡም ጠቁመዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ጨምሮ ከ151 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን በአዲስ እና በነባር ለማስተማር መታቀዱን በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!