
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንድ ቀን የሚቆየው የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡ በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ እየመከረ የሚገኘው ምክር ቤቱ ከኃይል አማራጭ በዘለለ ፖለቲካዊ ውይይት እንደሚያስፈልግ አመላክቷል፡፡
በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ሕዝብ በተደጋጋሚ ማሳሰቡን የምክር ቤት አባላት አንስተዋል፡፡ የዘገየውን የሕዝብ ጥያቄ የጠለፉት ኃይሎች ደግሞ የግጭቱ ተዋናይ ኾነው ብቅ ማለታቸውን ነው የምክር ቤቱ አባላት ያነሱት፡፡
ከለውጥ ማግስት የተፈጠረው ሀገራዊ የፖለቲካ ሥነ-ምህዳር የአማራን ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ የመመለስ እድል ፈጥሯል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት እንዳለመታደል ኾኖ “በድል ማግስት ላይ ቆመን በበደል ትርክት ተይዘናል” ብለዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች ለሕዝብ የገቡትን ቃል አለመመለሳቸው ቅሬታ መፍጠሩን እና ለግጭት መዳረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የሕዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ሕዝብም ከመንግሥት ጎን በመሆን የሰላም አማራጭን መፍትሔ አድርጎ መውሰድ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት በሀገራዊ የፖለቲካ መድረክ የሚወክሉ መሪዎችን እረፍት ከመንሳትና ልማትን ከመጉዳት የዘለለ ትርጉም እንደማያመጣም ገልጸዋል፡፡
ክልሉ አሁን የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ያለፉትን ጊዜያት በሰከነ ኹኔታ ኦዲት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አባላቱ አንስተዋል፡፡
ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የተፈጠረው ግጭት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ነፍጥ ያነሱ የትኞቹም ኃይሎች ወደ ጠረንጴዛ ተመልሰው መነጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!