የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ እስካሁን ያከናወናቸውን ሥራዎች እና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ይፋ አደረገ።

61

ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ እስካሁን ያከናወናቸውን ጅምር ስራዎች እና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ይፋ አድርጓል፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ነጃት ግርማ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ አዋጁ ከታወጀበት ቀን አንስቶ ቦርዱ እስከተቋቋመበት ድረስ በነበረው የአፈፃፀም ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡

በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምር ጠቅላይ መምሪያ ማዕከል በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ተጠርጣሪዎች ያሉበትን ሁኔታ መኝታ ክፍል ድረስ በመግባት ምልከታ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ከጠተርጣሪዎች ጋርም እንዲሻሻልላቸው በሚፈልጓቸው ጉዳዮች እና እንደ ችግር ባነሷቸው

ነጥቦች ላይ በስፋት ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ተጠርጣሪዎቹ ያነሷቸውን ጉዳዮች በመያዝ ከማዕከል አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ መመከሩን ጠቁመዋል፡፡

በእለቱ በተደረገ ምልከታም የተጠርጣሪዎቹ ሰብዓዊ መብት አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አይተናል ብለዋል ምክትል ሰብሳቢው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ዜጎች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየታሰሩ ነው የሚለውን ለማረጋገጥም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፊትም ሆነ በኋላ መደበኛ የሕግ ማስከበር እና ወንጀል የመከላከል ሥራ ከአስቸኳይ ጊዜ አውድ ውጪ እየተገበሩ እንዳለ እንደተገለጸላቸው ማብራራታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ክልሎች የሚፈልሱትን መታወቂያ የሌላቸውን ማጣሪያ ለማድረግ ፣ የጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን ብዙ ጊዜ ለወንጀል ድርጊት ማስፈፀሚያነት መገልገያ ስለሚደረጉ ፣ በመደበኛ የወንጀል መከላከል ስራ እንደሚያደርጉት አንድ ቦታ አቆይተው ወደ የአካባቢያቸው የሚመለሱትን እየመለሱ ሌሎችን በከተማ አስተዳደሩ ወደተዘጋጀው የማገገሚያ ማዕከል እንደሚያስገቡ ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ወቅት አንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ለጊዜያዊ ማቆያነት ተጠቅመው እንደነበር ፤ አሁን ላይ ግን ምንም ዓይነት ሰው በየትኛውም ትምህርት ቤት የለም የሚል ምላሽ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ለሕዝብ ጥቆማ ነጻ የስልክ መስመር ቁጥር 8557 ተከፍቷል፣ በነጻ የስልክ መስመር፣ በአካልና በጽሁፍ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ወቅት የሚስተዋሉ ማናቸውም ችግሮችን መጠቆም እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በአማራ ክልል ላይ በመዘዋወርና የአዋጁን አፈፃፀም በመፈተሸ በአጠቃላይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የተያዙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥር፣ በስም እና ምክንያት እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ በዝርዝር ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዞኑ በተፈጠረ የሰላም እጦት ችግር በፀጥታ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next articleሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የሰላም አማራጭን መፍትሄ አድርጎ እንዲወስድ የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።