
የሕግ ክፍተቱ መስተካከል እንዳለበት ደግሞ በሕግ ዙሪያ የሚሠሩ አካላት ተናግረዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 22/2012ዓ.ም (አብመድ) በመኖሪያ ቤት ሠራተኛነት ከሚተዳደሩት ታዳጊዎች መካከል አበባ ይግዛው እና ነፃነት መንገሻ ለአብመድ እንደገለፁት የቤት ሠራተኝነት ሙሉ ጊዜን በሥራ ላይ ማሳለፍ ከመሆኑም በላይ ነፃነት የሌለው፤ መብት የማይከበርበት ሥራ ጭምር ነው፡፡
አሠሪዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳይናኙ ስለሚፈልጉ ሞባይል የመጠቀም፣ ማኅበራዊ ግንኙነት የመፍጠርና ትምህርታችንን በአግባቡ የመማር ዕድሎችን እንደሚነፍጓቸውም ነው የተናገሩት፡፡ በቤት ውስጥም ቢሆን የንጽህና መጠበቂያና የመመገቢያ ጊዜ በአግባቡ እንደማይሰጣቸውም ተናረዋል፡፡ ከዚህም በላይ በሥራ ላይ ለተሰበረ ዕቃ ከደመወዝ ገንዘብ የመቁረጥ፣ ድብደባ እና ሌሎችም የአካልና የሞራል ጉዳቶች እንደሚደርሱባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደ መፈትሔ የምንወስደው ሌላ ቤት ተቀጥሮ መሥራትን ነው፡፡ መብትና ግዴታችንን የምናስከብርበት ሕግ ይኑር አይኑር አለማወቀችንም ያሳስበናል›› ብለዋል፡፡ አንዳንድ ቀጣሪዎች ደግሞ ሠራተኞቻቸውን ልክ እንደልጆቻቸው የሚንከባከቡም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ሣራ ተገኝ ይባላሉ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዳግማዊ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ‹‹የቤት ሠራተኛየን በውል ነው የቀጠርኳት፤ የምንኖረውም በሠላምና በፍቅር ነው፡፡ ልጆች የአሳዳጊዎቻቸውን ባሕሪ ስለሚወርሱ የቤት ሠራተኛየን መበደል ልጅን እንደ መበደል ነው፡፡ እርሷ ካልጠገበች ልጀንም አታጠግባትም፣ እርሷ ንጹህ ካልሁነች እንደዚሁ ልጄም ትቆሽሻለች፤ በመሆኑም ሠራተኛን መንከባከብና ፍቅር ማሳየት ለራስ ነው›› ብለዋል ለአብመድ በሰጡት መረጃ፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሥራ ስምሪትና ሠላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ደሳለኝ እንደገለፁት የኢፌዴሪ አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2ዐ11 በቤት ውስጥ ስለሚቀጠሩ የቤት ሠራተኛ፣ የቤት ዘበኛ፣ የግል መኪና ሾፌርና የመሳሰሉት በአሠሪዎቻቸው መካከል የሚደረግን ውል በተመለከተ ‹‹ሚኒስቴሩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመመካከር በቤት በሚሠሩ ሠራተኞች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑትን የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎችና የሚፈፀሙበትን አኳኋን መመሪያ ያወጣል›› በሚል የታለፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጽሕፈት ቤታቸው የኢንዱስትሪ ግንኙነት ያላቸው ሆቴሎች፣ ፋብሪካዎችና ለትርፍ የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ላይ ይህንን አዋጅ ተፈፃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
እንደቡድን መሪው ገለፃ የቤት ሠራተኞች በቀጣሪዎቻቸው በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ በደል ይደርስባቸዋል፡፡ ለነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ወደፊት ደንብና መመሪያ ሊወጣ እና ሰፊ የንቃተ ሕግ ትምህርት ሊሰጥበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ ደነቀው ካሳዩ (ቀሲስ) ደግሞ የቤት ሠራተኞችን በተመለከተ ቀደም ሲል በነበረው የኢፌዴሪ አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996ም ሆነ በተሻሻለው 1156/2ዐ11 ያልተካተቱ በመሆናቸው በደል እየደረሰባቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የሕግ ክፍተቱ ቢኖርም ‹‹ሲቀጠሩ ውል ይዘው ከሆነ ጉዳት ሲደርስባቸውና ገንዘብ ሲቀሙ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ካቀረቡ የጉዳት ካሳቸውን እናያለን፡፡ ነገር ግን ‹ያለ አግባብ ተባረርን፣ ተንገላታን› ብለው ቢመጡ በሕግ የረቀቀ አስገዳጅ ውል ባለመኖሩ ምክንያት ምንም መፍትሔ አያገኙም ነው›› ያሉት፡፡ ለነዚህ ወገኖች ደንብና መመሪያ ሊወጣላቸው እንደሚገባና የቤት ሠራተኞችም በመኖሪያ ቤት ሲቀጠሩ ውል ይዘው መሆን እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመንሽ አዱኛ