
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ከመደበኛ ሥራቸው ተሥተጓጉለው ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በመምጣቱ በማኅበራት መካዝን ውስጥ የተገኘውን ግብዓት መከፋፈላቸውን አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር በላይነህ ኀይሉ በደራ ወረዳ የገረገራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ኑሮአቸውን የሚመሩት ከግብርና ምርት በሚያገኙት ምርት ብቻ ነው፡፡
አርሶ አደር በላይነህ የግብዓት እጥረቱ በምርታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ይላሉ፡፡
ማዳበሪያው በወቅቱ ባለመድረሱ አርሶ አደሩ ለአላስፈላጊ ወጭ እየተዳረገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሌላ ቦታ ማዳበሪያ እየተሸጠ ነው የሚለውን ወሬ ተከትሎ አርሶ አደሮች ግብዓት ለማግኘት መደበኛ ሥራቸውን በመተው ሲንቀሳቀሱ እንደሚውሉም ተናግረዋል፡፡
አርሶአደሩ በአካባቢያቸው ያለው የሰላም ኹኔታ የግብዓት እጥረቱ እንዲባባስ እያደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ማዳበሪያ (ዩሪያ) አለመቅረቡ ደግሞ ሰብሉ ቀጭጮ እንዲቀር ማድረጉን አንስተዋል፡፡ የማዳበሪያ እጥረቱን ለመቅረፍ የሚመለከተው አካል ሰላሙን በማስከበር በኩል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ሁሉም አካል ነገ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ተመልክቶ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በውይይት በመፍታት ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ሊቀርፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አርሶ አደር የማታ ቢሠጥ የፋርጣ ወረዳ ሳህርና ቅፍናጥ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡
የልጆቻቸውን ሕይወት ለማቃናት እና የተሻለ ኑሮ ለመኖር የእርሻ ሥራቸውን አጥብቀው ይዘዋል፡፡
መሬታቸው ያበቀለውን አንጓለው አበጥረው ለልጆቻቸው ይመግቡ ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን በክልሉ ውስጥ በተለያዬ አካባቢ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በአግባቡ ምርታማ ለመኾን እክል ፈጥሮባቸዋል፡፡
በተለይ ግብዓት በሚፈለገው መጠን አለመቅረቡ ችግር ኾኖባቸዋል፡፡
ዛሬ በተደረገ እንቅስቃሴ እያንዳንዱ በወረዳው ውስጥ የሚገኝ ኅብረት ሥራ ማኅበር 150 ኩንታል ተከፋፍሏል፡፡
ይህም ለአርሶ አደሮች በፍትሓዊነት ለአስር አንድ ኩንታል እንደተከፋፈሉ ይናገራሉ፡፡
አርሶ አደር የማታ እንዳሉት በተለይ ለጠላ፣ ለበሶ፣ ለቆሎ፣ ለገንፎ እና ለአጥሚት የሚያገለግለው የክንክና ገብስ የሚዘራ ከጳጉሜ ወር ጀምሮ ቢኾንም ማዳበሪያ ባለመቅረቡ ሥጋት ላይ መኾናቸውን ያነሳሉ፡፡
አርሶ አደሮች በሥራ ችግራቸውን ለመቅረፍ ቢታትሩም የማዳበሪያ እጥረቱ ሊያላውሳቸው እንዳልቻለ አንስተው ለቀጣዩ ዓመት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የግብዓት እጥረቱ እንዲፈታ ሰላሙን በማረጋገጥ በኩል ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!