
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንድ ቀን የሚቆየው የአማራ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡ በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የክልሉን ሕልውና አደጋ ላይ የጣለ ሆኖ ስለተገኘ የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ለፌዴራል መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታዎጁን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ እና የኮማንድፖስቱ አባል አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት የመነሻ ሃሳብ ላይ ገልጸዋል፡፡
“በክልሉ የተፈጠረው ወቅታዊ ግጭት ድህረ ጦርነት የፈጠረው ልዩነት ነው” ያሉት አቶ ደሳለኝ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡ ካለፈው ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ እየተስተዋለ የመጣውን የክልሉን የሰላም እና ጸጥታ ችግር በክልሉ አቅም ለመፍታት የታየው ዳተኝነት እና የአመራሩ የተዛነፈ እይታ ችግሩ ውሎ ሲያድር አቅም እንዲያገኝ እና ከክልሉ መንግሥት አቅም ውጭ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡
በተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች መንግሥታዊ የአሠራር ሥርዓት እንዲቋረጥ አድርጓል ያሉት አቶ ደሳለኝ የመከላከያ ኃይል ቀድሞ ወደ አካባቢው መድረስ እና የሕዝቡ አስተዋይነት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ አድርጓል ነው ያሉት፡፡ እንደዚያም ሆኖ በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ በክልሉ ውስጥ እየተስተዋለ የመጣው ዋልታረገጥ ልዩነት፣ የሕዝብ ጥያቄዎች አለመመለሳቸው የፈጠረው ብሶት እና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የፈጠረው የሥነ-ልቦና አለመረጋጋት የፈጠሩት ችግር እንደሆነ ያነሱት አቶ ደሳለኝ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የሚያመርቱ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት አቀጣጣይነትም ተስተውሎበታል ብለዋል፡፡
ኮማንድፖስቱ ከታወጀ ማግስት ጀምሮ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ሰላም መታየቱን ያወሱት አቶ ደሳለኝ አሁንም ቀሪ ሥራዎች በመኖራቸው የኦፕሬሽን ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች የግጭት አማራጭን በመተው ለሰላማዊ ትግል እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ የሰላም አማራጮች አሁንም በሮቻቸው ዝግ አይደሉም፤ የሚፈለገው የሰላም አማራጭ ከተገፋ ግን ሕግን የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ የማስከበር ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን ሰላም በክልሉ እየታየ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በክልሉ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ስላለው በአጠረ ጊዜ የክልሉን ሰላም አረጋግጦ ወደ መደበኛ አሠራር መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ለማረጋገጥ፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር ሪፎርም ለመስራት እና የኮማንድፖስቱን እወጃ ከተያዘለት ጊዜ ለማሳጠር የክልሉ ሕዝብ፣ የጸጥታ ኃይሎች እና የምክር ቤቱ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ ደሳለኝ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!