“የተፈጠረው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ክፉኛ ለችግር ዳርጎናል” የቀን ሠራተኞች

35

ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “መንገድ ሲዘጋ አብሮ የሚዘጋው ጉሮሮዬ ነው፣አንድ ቀን ሳልሠራ ካልዋልኩ አንድ ቀን ሳልበላ እውላለሁ ማለት ነው” በባሕር ዳር ከተማ በቀን ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ የተናገሩት ነው። የሰላም እጦት የሚፈጥረው ሁለንተናዊ ምስቅልቅል ማኀበራዊ እረፍት የሚነሳ፣ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን የሚያስተናግድ፣ የሰውን ልጅ በሕይወት የመኖር እና ያለመኖር የሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል የጉስቁልና መንገድ ነው። እናም ሰላምን መምረጥ የሚገባን፣ ሰላምን የምንፈልገው የሕልውናችን ዋስትና ስለኾነ ነው።

በአማራ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ አለመረጋጋትና የሰላም እጦት የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ፈተና ላይ ወድቆ፣ እንደ አዘቦቱ ጊዜ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ መብላት አለመቻል በተለይም ውዱን የሰው ሕይወት ቀጥፎ አልፏል። በአማን ጊዜ ሠርተው በቋጠሯት ሳንቲም የእለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑ የቀን ሠራተኞች የተፈጠረው አለመረጋጋት ክፉኛ ለችግር እንደዳረጋቸው ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። በቀን ሥራ ሙሉ ወጫቸውን የሚሸፍኑ የቀን ሠራተኞች እንደሚሉት ሠርተን የቤት ኪራይ መክፈል፣ ሠርተን መብላት መጠጣት ፣ ሠርተን ቤተሰብ መምራት ፣ ልጅ ማሳደግ በአንድ ቀን የመሥራትና አለመሥራት ላይ የተወሰነ ነው ይላሉ።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት በባሕር ዳር ከተማ ተፈጥሮ በነበረው የእንቅስቃሴ መገታትና የሰላም እጦት “ለልጄ ዳቦ መግዛት እንኳን አልቻልኩም ነበር” ይላሉ። በቀን ሥራ ቤተሰብ እንደሚመሩ የነገሩን ግለሰብ እንደሚሉት የልጆች አባት ናቸው። ባለቤታቸውም ቤቱን የሚመሩት፣ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እሳቸው በቀን ሥራ ሠርተው በሚያመጧት ገንዘብ ነው። “መንገድ ሲዘጋ አብሮ የሚዘጋው ጉሮሮዬ ነው” የሚሉን ግለሰቡ እንደ ሃብታሞች መንገድ ስለሚዘጋ ብዬ አስቤዛ ቀድሜ አላስቀምጥ ነገር ከእጅ ወዳፍ የኾነው ኑሮዬ በአንድ ቀን መሥራትና አለመሥራት ላይ የተወሰነ ነው ይላሉ። ዛሬ አልሠራሁም ማለት ነገ ብቻ ሳይኾን ዛሬንም ጭምር አልበላም ማለት ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ በተፈጠረው የሰላም እጦት የተቸገሩ አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩትም “በአንድ በኩል ሥራ ማጣት ይፈትነናል ፣ እንደምንም የተገኘችውን ሥራ በሰላም እጦት ምክንያት ከሥራ ውጭ መኾን ግን የበለጠ ከባድ ነው” ይላሉ። “ነገ ሠርቼ እክፍላለሁ” ብሎ ተበድሮ መብላትን ጭምር ነው የሚያሳጣን ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

በእርግጥ የሰላም እጦት አይደለም ሠርቶ መብላትን ለምኖ ለመብላት እንኳን እድል አይሰጥም ይላሉ ሠራተኞቹ። በሰላም እጦት ሁሉም ሰው ሰለባ ቢኾንም የሚያሳርፈው ጠባሳ ግን ይለያያል ባይ ናቸው። እናም የሰላምን ዋጋ በመረዳት ፣ በሰላም እጦት የሚፈጠረውን ጉስቁልና እና ሁለንተናዊ ውድቀት በመገንዘብ ሰላምንና መመካከርን፣ ችግሮችን በውይይት መፍታትን የሚያስቀድም ኹኔታ እንዲፈጠርም አጥብቀው ጠይቀዋል።

የሰላም እጦት ከሰላማዊ እንቅስቃሴ እስከ ሕልውና የሰውን ልጅ የሚፈትን ጉዳይ ነው። የሰላም ባለቤቱ ሰው ነው ፣ በይበልጥ የሰላም እጦቱ ምክንያትም ሰው ነው ፣ ሰለባውም ሰው ነው። እናም ለሰላም መስፈንና ሰላማዊ እንቅስቃሴን ለማምበር በሰከነ መንገድ ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ።
ሀገር አማን ውሎ ሲያድር ነው የዜጎች ሕልውና የሚሰምረውና ለሰላም ዘብ መኾንም ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተመስርቶ በመሆኑ ኃይል ማሰባሰብን የሚያስችለውን የሰላም አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል” ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ
Next article“አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ የማስከበር ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰላም በክልሉ እየታየ ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው የኮማንድ ፖስቱ አባል