“የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተመስርቶ በመሆኑ ኃይል ማሰባሰብን የሚያስችለውን የሰላም አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል” ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ

106

ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡ አስቸኳይ ጉባዔውን የከፈቱት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋየ የክልሉ አሁናዊ ሁኔታ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል ያሉት አፈ-ጉባዔዋ የተፈጠረው ጉዳት የክልሉን ሕዝብ ለከፋ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማሕበራዊ ጉዳት የዳረገ ነበር ነው ያሉት፡፡ ችግሩን በማባባስ እና በማቀጣጠል የውጫዊ ኃይሎች እጅ የለበትም ባይባልም መሰረታዊ ምክንያቶቹ ውስጣዊ አንድነትን ካለማጽናት የመነጨ ነበር ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጥያቄዎች በግልጽ ተለይተው ያደሩ እና ስልጡን ትግል እየተካሄደባቸው ያሉ ናቸው ያሉት አፈ-ጉባዔዋ ችግሮቹን ለመፍታት ግን ግጭት በፍጹም የመፍትሄ አማራጭ ሆኖ መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተመስርቶ በመሆኑ ኃይል ማሰባሰብን የሚያስችለውን የሰላም አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በርካቶቹ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የጋራ ጥረት በመሆኑ ሕዝብን ለቁጣ የዳረጉ ጥያቄዎች በፍጥነት መመለስ ይኖርብናል ያሉት አፈ-ጉባዔዋ “ችግሮቻችን እንድናይ ሕዝብ እድል ሰጥቶናልና በአግባቡ መጠቀም ይገባል” ብለዋል፡፡ ለአንድ ቀን የሚቆየው የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባዔ በክልሉ የተፈጠረውን ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች በብስለት፣ በጥልቀት እና በአስተዋይነት ገምግሞ መፍትሄ አመላካች ምክረ-ሃሳብ ያመነጫል የሚል እምነት እንዳላቸው አፈ-ጉባዔ ፋንቱ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ወደ አንጻራዊ ሰላም ተመልሷል” ነዋሪዎች
Next article“የተፈጠረው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ክፉኛ ለችግር ዳርጎናል” የቀን ሠራተኞች