
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን በተለይም በመንዝ፣ ማጀቴ እና በሸዋሮቢት አካባቢዎች ግጭትና አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ተቋማት ሰላም የማስፈን ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። የማጀቴ ነዋሪዎች ለአሚኮ እንደገለጹት አሁን ላይ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል። የንግድ ቤቶች እና የመንግሥት ተቋማት ተከፍተው በመደበኛ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ባንክ ቤቶች፣ ካፌ እና ምግብ ቤቶችም ወደ መደበኛ አገልግሎት ተመልሰዋል።
የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉትም ከተማዋ በተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለች። በግጭቱ ወቅት የግል እና የመንግሥት ተቋማት በመዘጋታቸው ለእንግልት ተዳርገው እንደነበር የሚያስታውሱት ነዋሪዎች አሁን ላይ ግን ተቋማት እና ሠራተኞቻቸው በመደበኛ ሥራቸው ላይ ይገኛሉ ብለዋል። የተገኘው ሰላም ዘላቂ ኾኖ በሙሉ ልብ ወደ ልማት ለመግባት ሕዝቡ ከጸጥታ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ ለጋራ ሰላም መሥራት እንደሚያስፈል ነዋሪዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ግጭት እና አለመረጋጋት ከገጠማቸው የዞኑ አካባቢዎች መካከል መንዝ አንዱ ነው። አካባቢው ከግጭት ወጥቶ ወደ ወትሮው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱንም ከነዋሪዎች አረጋግጠናል። “አሁን ላይ ሕዝብ እንዳይረጋጋ ኾን ተብሎ ከሚወራው አሉባልታ ውጭ አንዳች የሚያሰጋ ችግር የለም” ሲሉ ነው ያነጋገርናቸው የመንዝ ነዋሪ የገለጹት።
አሉባልታዎችን ወደ ጎን በመተው ለሰላም እና ለልማት መሥራት ይገባል ሲሉም ነዋሪው መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!