በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚታየውን ስርቆት ለመከላከል ‘የኢንድስትሪ ፖሊስ’ በመተግበር ላይ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

241

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 22/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የመሠረተ ልማት ኮሚቴ በክልሉ የመሠረተ ልማቶች ግንባታ የደረሱበት ደረጃ፣ ችግሮች እና መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ባደረገው ውይይት እንደተገለጸው ከአንደኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጀምሮ ግንባታቸው የተጠናቀቁ መንገዶች 25 ናቸው፡፡ መንገዶቹም 2ሺህ 14 ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ፡፡

780 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 10 መንገዶች ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት የርእሰ መስተዳድሩ የመሠረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ ደሣለኝ አስራደ እንደገለጹት አሁን በግንባታ ላይ የሚገኙ 28 ናቸው ይህም 1 ሺህ 528 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ፡፡

በ2011 ዓ.ም የጨረታ ሂደታቸው ተጠናቅቆ ለተቋራጭ የተላለፉ 13 ፕሮጀክቶች ናቸው፤ 633 ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ በ19 ቢሊዮን 479 ሚሊዮን 887 ሺህ 622 ነጥብ 81 ብር የተላለፉ መሆናቸውን አቶ ደሣለኝ አስራደ ጠቁመዋል፡፡

የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶቹ ፈጥነው ወደ ሥራ አለመግባታቸው፣ ከተጀመሩ በኋላም በተለያዩ ምክንያቶች መጓተታቸው፣ የግንባታ ጥራት ችግር እና የመንገዶች ደረጃ አወሳሰን የቅሬታ ምንጭ መሆኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡

እላፊ የመጠቀም ፍላጎትና ለመንገድ ሥራው ሁሉም ተባባሪ አለመሆን፣ ትክ ወይም ካሳ ተቀብለው እያለ ቦታውን ያለማስረከብ ወይም የተሠራን ግንባታ ለማፍረስ መሞከር፣ በካሳ የተሰጠን ገንዘብ ለላቀ ልማት ያለማዋል እና ገንዘቡ ሲያልቅ ቦታውን ለማስረከብ ማቅማማት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ ነው አቶ ደሣለኝ የገለጹት፡፡

የሚገነቡት መንገዶች ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው በመሆኑ ማኅበረሰቡ እንቅፋት ከመሆን ተቆጥቦ አጋርነትን ማሳየት እንደሚጠበቅበት የመሠረተ ልማት ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል፡፡

በፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ በክልሉ መንግሥት የሚገነቡ መንገዶች ከተደራሽነት አንፃር ፍትሐዊ እንደሆኑ እና ሁሉንም ዞኖች ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ በውይይቱ ተገልጧል፡፡ ከእቅድ ጀምሮ አስከ ክንውን ድረስ ሁሉም መንገዶች ከአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ማኅበረሰብ ጋር በጋራ ተባብሮ የመሥራቱ ሂደት አበረታች መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በክልሉ የኔት ወርክ መቆራረጥና የአገልግሎት ጥራት ችግር በስፋት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮ-ቴሌኮም ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር አገልግሎቱ የተሳሰረ በመሆኑ ኃይል ሲቋረጥ ባንክን ጨምሮ በኢንተርኔት ሥራቸውን የሚያስኬዱ ድርጅቶች እንደሚስተጓጎሉ ነው የተገለጸው፡፡ በአማራ ክልል ሁለት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ እና 563 ቀበሌዎች የኔት ወርክ አገልግሎት ፈጽሞ የሌላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የሰሜን ሰሜን ሪጅን ሥራ አስኪያጅ ያረጋል ደምሴ ‹‹የኔትወርክ አገልግሎትን ለማሻሻል ተጨማሪ ኬብል ብንዘረጋም በተደጋጋሚ ይሰረቃል፤ ንብረታችንም ይወድማል፣ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ቢሰጥም ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሆኗል፡፡ ተደራሽነትን ለማስፋት ስንሠራ ሠራተኞቻችን ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው›› ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል የመሠረተ ልማት ኮሚቴ ከተወያየባቸው ጉዳዮች ውስጥ በክልሉ በገጠርም ሆነ በከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ ሽፋኑን ለማሻሻል እንዲሁም በመስኖ ልማት አሁን ከደረሰበት ደረጃ ከፍ ለማድረግና የአርሶ አደሩን በመስኖ የማልማት አቅም ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ይሁን እንጅ የውኃ መገኛ ቦታ ልየታ ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ፣ ወደ ተግባር ተገብቶ የቁፋሮም ሆነ የግንባታ ሥራው ከተጠናቀቀ ወይም በከፊል ከተሠራ በኋላ ውኃ የማይገኝባቸው ሁኔታዎች አሉ፤ በመሆኑም በተጠቃሚው ማኅበረሰብ የቅሬታ ምንጭ ስለሆነ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት ተገቢ ጥናት መደረግ እንዳለበት እና ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
ብዙ የውኃ ቁፋሮዎች እና ግንባታዎች በወቅቱ እንደማይጠናቀቁ፤ የተጠናቀቁትም ቶሎ ወደ ሥራ መግባት ባለመቻላቸው ኅብረተሰቡን ቅሬታ ውስጥ እንዳስገባ ተገልጧል፡፡

የባቡር መንገድ መሠረተ ልማትን በተመለከተ፣ አዋሽ-ወልዲያ -ሀራ ገበያ መንገድ ግንባታ በአማራ ክልል እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክትም እንደ ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዘ ችግር የሚስተዋልበት ነውም ተብሏል፡፡ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ የሚገኘውም የተዘረጉ የባቡር መሠረተ ልማቶችን መስረቅና መዝረፍ ነው፤ በተለይ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር እና ሰሜን ሸዋ ዞን(ኤፍራታ ግድም ወረዳ) ችግሩ ጎልቶ ይታያል ተብሏል፡፡

የአይሮፕላን ማረፊያ መሠረተ ልማትን በተመለከተ፣ በ2011 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ይሠራል ተብሎ በእቅድ የተቀመጠ ቢሆንም በበጀት እጥረት ምክንያት ለ2012 ዓ.ም ተላልፎ አሁን መሬት ነፃ አድርጎ ለማሥረከብ ወደ ሥራ መገባቱን አቶ ደሣለኝ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጥበበ ኃይሉ ‹‹አንድ ፕሮጀክት ለመገንባት ሲታሰብ የፀጥታው ጉዳይ አብሮ መታሰብ አለበት›› ብለዋል፡፡ የመብራት እና የቴሌ ፕሮጀክቶችን የማኅበረሰቡን ተሳትፎ በማንቃት ጥበቃ እያደረጉ እንደሆኑ ምክትል ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡ በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ‘ኢንድስትሪያል ፖሊስ’ን በመተግበር ላይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንድስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል መንገድ ብቻ ሳይን ሁሉንም ሥራዎች በወቅቱ መሠራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በየደረጃው ያለኃላፊ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማንቃት የሚሰተዋለውን የፀጥታ ችግር፣ የስርቆት ወንጀል፤ የባለሙያዎችን መብት ማስከበር አለበት ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleበአማራ ክልል ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሊጠበቅ የሚገባው የተፈጥሮ አካባቢ መኖሩን የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ጠቆመ፡፡
Next articleበ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ፋሲል ከነማን ከባሕር ዳር ከነማ ያገናኛል፡፡