“በሰላም መደፍረስ ምክንያት የተሟላ ድጋፍ ባለማግኘታችን ችግር ላይ ወድቀናል” በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች

96

ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአካባቢው በተከሰተው ሰላም መደፍረስ ምክንያት ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረግ ማቆማቸውን በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡

አስተያየት ሰጭዎች እንዳሉት ነሐሴ/2015 ዓ.ም መጀመሪያ 15 ኪሎ ግራም በቆሎ በመንግሥት ቀርቧል፡፡

ይሁን እንጂ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ በጎ ፈቃደኞች ሲያደርጉት የነበረው ድጋፍ በመቆሙ ተፈናቃዮች በተለይም ደግሞ እናቶችና ሕጻናት ችግር ላይ መውደቃቸውን ነው ያነሱት፡፡

በቀጣይም አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላሙ ተመልሶ በቂ ድጋፍ ማድረግ ካልተቻለ በሕጻናትና እናቶች ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ሊኾን እንደሚችል አንስተዋል፡፡

በአካባቢው የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በሕጻናትና እናቶች የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱንም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባያብል እንዳሉት በክልሉ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ድጋፍ ለማድረግ አስቸግሯል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በመጠለያ ጣብያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሁለት ወር ድጋፍ መመደቡን ያነሱት ኮሚሽነሩ ከተመደበው ውስጥ ለተወሰኑ ተፈናቃዮች እንደቀረበ በጦርነቱ ምክንያት መቋረጡን ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮች አሁን የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት መንግሥት የአካባቢውን ሰላም የመመለስ ሥራ እየሠራ በመኾኑ በቅርቡ በተገቢው መንገድ ድጋፉ እንደሚደርስ አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ማኅበረሰቡም ለሰላሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቻይና መንግስት በሰጠው የነፃ ትምህርት እድል አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች ሽኝት ተደረገ።
Next articleበሰላም እጦት ምክንያት የግብርና ግብዓቶች በሚፈለገው ልክ ለአርሶ አደሩ ባለመድረሳቸው በምርታማነቱ ላይ ተፅዕኖው ከፍተኛ እንደኾነ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።