“ኢትዮጵያ ብሪክስን (BRICS) ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ የዲፕሎማሲያችን ድል ማሳያ ነው!” የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

78

ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ብሪክስ (BRICS) ሕብረትን ተቀላቅላለች፡፡

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱት “ብሪክስ” የተባለው የሀገራት ሕብረት፤ 32 በመቶ የሚኾነውን የዓለም ኢኮኖሚ የጥቅል ምርት አቅም በእጃቸው ያደረጉ ሀገራት ያሉበት ስብስብ ነው፡፡ ይህ ስብስብ ራሱን የቻለ አዲስ የልማት ባንክ ያቋቋመ ሲኾን፣ ፍትሐዊ ዓለምአቀፍ የኃይል አሰላለፍ እንዲኖር በማለም የተመሠረተ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ 40 ሀገራት ይህንን ስብስብ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ግብፅ፣ ኢራን እና አርጀንቲና ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ስብስቡን ተቀላቅለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ስብስብ መቀላቀሏ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኝላታል፡፡ በዓለምአቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከማሳደግም በላይ የተለያዩ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች በቡድኑ የልማት ባንክ በኩል ፋይናንስ እንዲያገኙ በር ይከፍታል፡፡ ነባር የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ባሻገር አማራጭ የፋይናንስ ምንጭም ይገኝበታል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በዘላቂነት ከመቅረፍ አንፃር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል የሚኖረው የንግድ፣ የባህል እና የፖለቲካ ቁርኝት የላቀ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመኾኑ፤ ኢትዮጵያም የዚህ ስብስብ አባል መኾኗ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖዋን የበለጠ የሚያሳድግ እንደሚኾን ይጠበቃል፡፡

ከኢንቨስትመንት አኳያም የብሪክስ አባል ሀገራት የሚያደርጉት ትብብር ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ይኾናል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያም የብሪክስ አባልነት የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡

ሀገራችን ይህንን ስብስብ መቀላቀሏ በያዘችው የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ውጥን መሠረት የተከናወነ ሲኾን፤ የብሪክስ አባል ለመኾን ካመለከቱ በርካታ ሀገራት መካከል መመረጧም የሀገራችንን ዲፕማሲያዊ ጥረት ውጤት መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ በሂደቱ ድጋፍ ያደረጉትን ወዳጅ ሃገራት ኢትዮጵያ ታመሰግናለች።

የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ በቀጣይም ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን ታከናውናለች፡፡ ዓለምአቀፉን ተለዋዋጭ አካሄድ በመገምገም አዋጭ ስልቶችንም በቁርጠኝነት ማከናወኗን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያልገቡን እየገቡን፣ ችግሮችን እየፈታን፣ አንድ እየኾን ለልጆቻችን የኩራት ምንጭ የኾነች ኢትዮጵያን መፍጠር ይኖርብናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየቻይና መንግስት በሰጠው የነፃ ትምህርት እድል አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች ሽኝት ተደረገ።