
ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መኾኗን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ብሪክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ካሉ ስብስብ ኀይሎች መካከል በሕዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚ አቅሙና በመደመጥ አቅሙ እያደገ የመጣ ነው ብለዋል፡፡
የብሪክስ ስብስብ እያደገ ከመጣ በኋላ ከአርባ የማያንሱ ሀገራት ስብስቡን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከጠየቁት ሀገራት መካከል ሥድስት ሀገራት መመዘኛውን አሟልተው የብሪክስ አባል መኾን ችለዋል ነው ያሉት፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንደኛዋ ናት፡፡
የብሪክስ ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሕዝብ ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ኩራትና የዲፕሎማቲክ ድል ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስትመረጥ ታሪኳ፣ የሕዝብ ብዛት፣ ከፍተኛ እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗ ስለታመነበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ፣ በግብርና ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት እንዲሁም አጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ከፍተኛ መኾን፣ የኢትዮጵያ የመደመጥ አቅም ከፍ እያለ መምጣት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትኾን እንዳስቻላትም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ብሪክስ ማስገባት የብሪክስን እቅድ ለማሳካት ወሳኝ መኾኑ ታምኖበት መግባቷንም ገልጸዋል፡፡ ድሉ በብዙ ንግግር የተገኘ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትኾን ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ ላደረጉት እገዛ እናመሠግናለን ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾን ለአፍሪካም፣ በዓለም ላይ የመደመጥ አቅምም፣ ወሳኝ መኾኑን አምነዋል ብለዋል፡፡
ከቻይናው ፕሬዚዳንት ጋር በነበራቸው ቆይታ የእዳ ክፍያ ለአንድ ዓመት እፎይታ እንደሰጧቸውም ተናግረዋል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የብዙ ትብብር መስክ ስምምነት ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በወታደራዊ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት አብረን ለመሥራት ተስማምተናል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ ያላት፣ የወጣት ሀገር ናት፣ አሁን እየተመዘገበ ያለው ዘርፈ ብዙ ለውጥ ኢትዮጵያውያን በውል ባይረዱትም ዓለም በውል ተገንዝቦት እውቅና እየሰጠ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ዓለም በከፍተኛ አድናቆትና ምሥጋና እየተቀበለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ካስመዘገበቻቸው ወሳኝና የዲፕሎማሲ ድሎች ማካከል ብሪክስ አንደኛውና ዋነኛው ሊባል ይችላል ብለዋል፡፡
ወደ ብሪክስ መግባት ከአባል ሀገራቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ተደማጭነት ጠንካራ አድርጎታል፣ ይህ በጣም ትልቅ ድል ነው፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ድል ይቀጥላል፣ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፣ በአፍሪካ ትልቅ ተደማጭነት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ትኾናለች፣ ባልገባንባቸውና መግባት በሚገባን መድረኮች ሁሉ እየገባን ድምጿን ከሀገሯ በላይ በአህጉር እና በዓለም ደረጃ የምታስደምጥ ሀገር ትኾናለች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በውስጣችን ጥቃቅን ችግሮችና ያልገቡን ነገሮች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልገቡን እየገቡን፣ ችግሮችን እየፈታን፣ አንድ እየኾን ለልጆቻችን የኩራት ምንጭ የኾነች ኢትዮጵያን መፍጠር ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!