
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 21/2012ዓ.ም (አብመድ) አቶ አብርሃም አንሙት የ25 ዓመት ወጣትና የደጀን ወረዳ ሀገረ ሠላም ንዑስ ፍርድ ቤት ዳኛ ነው፡፡ ብር ለማውጣት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤ ቲ ኤም ማሽን ያመራል፡፡ ከእርሱ በፊት የነበረ የኤ ቲ ኤም ካርድ ተጠቃሚ ሲጠባበቅ ቆይቶ ወደ ሌላ የኤ ቲ ኤም ማሽን በመሄድ ብር ለማውጣት ይሰለፋል፡፡
አቶ አብርሃም ‹ኔት ወርኩ› ሲስተካከል የራሱን ኤ ቲ ኤም ለማስገባት ሲሞክር ማሽኑ ቀደም ባሉት ደንበኛ የታዘዘውን 4 ሺህ ብር ያወጣል፡፡ አቶ አብርሃም ቀድሞ ያዘዘው ግለሰብ ሌላ የኤ ቲ ኤም ማሽን ላይ ሲሰለፍ ዓይቶት ስለነበር በቀጥታ በመሄድ ‹‹ያዘዝከው ብር ስንት ነበር?›› ብሎ ጠይቆ 4 ሺህ ብር መሆኑን ሲያረጋግጥለት ብሩን ለባለቤቱ አስረክቧል፡፡
አቶ አብርሃምን ስለጉዳዩ ሲጠየቁም ‹‹እኔ ሙያዬ ይህንን እንዳደርግ ያስገድደኛል፤ ቤተሰቦቼም ሲያሳድጉኝ ያስተማሩኝ ይህንን ነው›› ብለዋል፡፡
ብሩን የተረከቡት የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው አቶ ነጋሽ ማንአህሎህ ‹‹ኔት ወርኩ ስላልሠራና አልወጣልኝ ስላለ ብር ለማውጣት ሌላ ማሽን ላይ ሄጀ ተሰልፌያለሁ፡፡ ‹ይህ ብር ያንተ ነው› ብሎ ሲሰጠኝ ማመን ተሳነኝ፡፡ በዚህ ዘመን ከወጣቱ እንደህ ዓይነት መልካም ሥራ በማየቴ ደስታዬ ወሰን የለውም›› ብለዋል፡፡ ሁሉም ሰው ከዚህ ወጣት ሊማር እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
መረጃውን ያደረሰን ጋሻዬ ጌታሁን ነው፡፡