“በከተማዋ የእንቁላልና የወተት ምርት ከበቂ በላይ እየቀረበ ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት

48

👉”በወቅታዊ አለመረጋጋትና ግጭት ምክንያት በገበያ እጦት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶብናል” ጥረት ወተት ልማት ማኅበር።

ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ አሥተዳደሩ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ለአሚኮ እንዳስታወቀው በከተማዋ 4 የወተት ልማት ማኀበራት በቂ የወተት ምርት እያቀረቡ ነው።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ መኖ ልማት ቡድን መሪ በለጠ መኳንንት እንደሚሉት የወተት ማኅበራቱ ከማምረትም በተጨማሪ ከ20 በላይ የመሸጫ ሱቆችን በመክፈት ለተጠቃሚ እያቀረቡ ነው።

በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችም ምርታቸውን ለተጠቃሚዎች በስፋት እየደረሱ ነው ተብሏል።

በዶሮ ማርባት ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ተስፋ ፍቅር እንደምትለው ለገበያው የሚመጥን በቂ የእንቁላል ምርት እያቀረበች ነው። የአንድ ቀን ጫጩቶችን ማሳደግ፣የእንቁላል ደሮዎችን ማርባት ፣እንቁላል በመሸጥ እንደምትተዳደር የገለጸችው ወጣት ተስፋ የመኖ ዋጋ መወደድ ለገበያ የምታቀርበውን የእንቁላል ዋጋ ለመጨመር አስገድዷታል። አንድ እንቁላል ከሰባት እስከ ስምንት ብር ይሸጥ የነበረው አሁን ላይ ከ9 ብር እስከ 10 ብር እየተሸጠ መኾኑን ነው የተናገሩት።

አቶ አጥናፉ ጌጡ ደግሞ የወረብ ጥረት ወተት ማኀበር ሊቀመንበር ናቸው። ማኅበሩ ከ270 በላይ ወተት አቅራቢ አባላት እንዳሉት የተናገሩት ሊቀመንበሩ ምርታቸውን በ9 ሱቆች ለተጠቃሚ እያደረስን ነው ብለዋል።

ከባሕር ዳር ከተማ በተጨማሪም በቀን እስከ 1200 ሊትር ወተት ወደ አዲስ አበባ ይልኩ እንደነበርም አንስተዋል።

በተፈጠረው ወቅታዊ አለመረጋጋት ግን በገበያ እጦት በወተት ምርታቸው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የተሰበሰበ 2500 ሊትር ወተት እንደከሰረባቸው የተናገሩት የማኅበሩ ሊቀመንበር በገንዘብ ሲተመንም ከ91ሺህ ብር በላይ እንደሚኾን ነው የገለጹት።

ማኅበሩ ከአባላቱ በቀን እስከ 2ሺህ ሊትር ይሰበስብ ነበር ፤ አሁን ላይ ግን ከ1 ሺህ ሊትር ያልበለጠ ነው እየሰበሰበ ለአካባቢው ተጠቃሚዎች የሚያደርሰው ብለዋል።

በመሸጫ ሱቆቹ ለተጠቃሚዎቹ በሊትር 50 ብር እየተሸጠ እንደኾነ የተናገሩት ሊቀመንበሩ ለወኪሎቻቸው ግን ከዚህ በቀነሰ ዋጋ እንደሚያስረክቡ ነው የተናገሩት።

የወተት ምርት በአንድ በኩል አምራቾች ከበቂ በላይ ምርት አለ ይላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዋጋ ውድነት ምክንያት ሸማች መጥፋቱ በገበያው ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው።

የከተማ አሥተዳደሩ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ መኖ ልማት ቡድን መሪ በለጠ መኳንንት ክፍተቱን ለመሙላት እየሠራን ነው ይላሉ።

የወተት ምርቱ በስፋት ለማኅበረሰቡ የሚደርስበትን ተጨማሪ መቸርቸሪያ ሱቆችን መክፈት፣ የዋጋ ትመና ማስተካከልና ሌሎችንም አማራጮች ለመጠቀም እየተሞከረ ነው ብለዋል።

አምራቾች ገበያ ፍለጋ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የሚልኩት ካላቸው ቋሚ ደንበኛ እጥረት ነው የሚሉት ቡድን መሪው የደንበኛ ቁጥሩን ለመጨመርም ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል። ለዚህም ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ውቧን የጎብኝዎች መዳረሻ ከተማ ባሕርዳርን የበለጠ ሰላሟ የተጠበቀ ለማድረግ እየሠራን ነው።” የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም መምሪያ
Next article“አለመግባባቶችን በሰከነ መንገድ መፍታት ይገባል” የደሴ ከተማ መንግሥት ሠራተኞች