
ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 በጀት ዓመት ከውጭ ሀገር ጎብኝዎቸ ከ107 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡
በበጀት ዓመቱም ከቱሪዝም ዘርፉ ከ237 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ቢገኝም አሁን ላይ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ መገታቱን መምሪያው ገልጿል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ሙሉዓለም አያና እንዳሉት ባሕር ዳር ከተማ በርካታ የተፈጥሮ፣ ሰው ሠራሽ ቅርሶች እና ሃይማኖታዊ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ናት። እንደ ጭስ አባይ፣ ጣና ሐይቅ፣ ዓባይ፣ በጣና ላይ የሚገኙ ገዳማት እና የከተማዋን ውበት ያላበሱ ዘምባባዎች ከመስህቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ወደ ላሊበላ፣ ጎንደር ቤተ መንግሥታት እና ሰሜን ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት ለሚጓዙ ጎብኝዎችም እንደ አንድ መዳረሻ በመኾን ታገለግላለች።
በኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት የቱሪስት ፍሰቱ መቀዛቀዝ ማሳየቱን ያነሱት ቡድን መሪው ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በነበረው ሰላም ዘርፉ ዳግም መነቃቃት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ከሚገኙት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባሻገር ጥርን በባሕርዳር፣ የጥምቀት በዓል እና ሌሎች የአደባባይ በዓላትን በማዘጋጀት የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ እንዲነቃቃ መደረጉን አንስተዋል፡፡
አቶ ሙሉዓለም እንዳሉት በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ በታየው ሰላም 193 ሺህ 324 የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል። ከ237 ሚሊዮን 166 ሺህ ብር በላይ ገቢም ተገኝቷል፡፡ ከጎብኝዎቹ ውስጥ 4 ሺህ 935 የውጭ ጎብኝዎች ሲኾኑ ከተገኘው ገቢ ውስጥ ደግሞ ከ107 ሚሊዮን 148 ሺህ ብር በላይ ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች የተገኘ መኾኑን ነው የገለጹት።
በ2015 ሐምሌ ወር ብቻ እንኳ 52 ሺህ የሀገር ውስጥ እና 415 የውጭ ጎብኝዎች ከተማዋን መጎብኘታቸውን ነው ቡድን መሪው ያነሱት፡፡
አቶ ሙሉዓለም እንዳሉት በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር በያዝነው ወር ወደ ክልሉ የሚደረገውን የቱሪስት ፍሰት ገትቷል፡፡ ክልሉን ለመጎብኘት ያቀዱ ጎብኝዎችም ጉዟቸውን ሰርዘዋል፡፡ ይህም በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ በዘርፉ ላይ መሰረት ያደረጉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ገቢ አሳጥቷል፡ በመንግሥት ገቢም ላይ ጫና አሳድሯል፡፡
ውቧን የጎብኝዎች መዳረሻ ከተማ ባሕርዳርን የበለጠ ሰላሟ የተጠበቀ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም መምሪያ ገልጿል።
የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍም ይሁን ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!