
ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የሚከሰተው የሰላም እጦት የትምህርት ዘርፉን እየጎዳው መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን ትምህርት ቢሮው “ትምህርት ለትውልድ” የሚል ንቅናቄ ጀምሮ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ንቅናቄው ጥሩ ሂደት ላይ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ንቅናቄው በሚፈለገው ልክ አለመሄዱን የተናገሩት ኀላፊው የሰላም ሂደቱ መሻሻል በማሳየቱ የተጀመሩ ሥራዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ለትምህርት ቀናዒ በመኾኑ ለትምህርት ሥራው ጥሩ አስተዋጽዖ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በርካታ ትምህርት ቤቶች በባለሀብቶች እና በልማት ድርጅቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ‘ትምህርት ለትውልድ’ ንቅናቄን በንቃት የማስቀጠልና የትምህርት ቤቶችን ግብዓት የማሟላት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ናቸው ያሉት ኀላፊው ሁልጊዜ ስለ ችግሮቹ ብቻ እያወሩ መሄድ አግባብ አይደለም፣ መቀየር አለባቸውም ብለዋል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለመቀየርም የክልሉን ሕዝብ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት፡፡ በትምህርት ወደኋላ መቅረት ትውልድን በእጅጉ እንደሚጎዳም አመላክተዋል፡፡ ትምህርት የክልሉ ሕዝብ የሕልውና ጉዳይ ነውም ብለዋል፡፡ በትምህርት ወደ ኋላ መቅረት በብዙ መንገድ ወደኋላ ያስቀራልም ነው ያሉት፡፡
ወጣቶች እና መላው የክልሉ ሕዝብ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መረባረብ ይገበዋልም ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በመተባበር በትምህርት ቤቶች ላይ የሚያጋጥሙ የግብዓት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡
አዳዲስ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ ያረጁ ትምህርት ቤቶችን በመጠገን ለመማር ማስተማሩ ምቹ ማድረግ ይገበዋል ነው ያሉት፡፡ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መጽሐፍት እንደሚሰራጩ የተናገሩት ኀላፊው መጻሕፍቱ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ሁሉም ሰው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡ መጻሕፍቱ የሁሉም ሀብት መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
የ8ኛ ክፍል ፈተና ታርሞ መጠናቀቁንምና ፈተና ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይገለጻል ብለዋል፡፡ ሁሉም ችግሮችን ተቋቁሞ ለትምህርት ሥርዓቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
የሰላም መደፍረስ የትምህርት ዘርፉን እንደሚጎዳው ያመላከቱት ኀላፊው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን የተፈተኑ ተማሪዎች ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተማሪዎች መመለሻ ትራንስፖርት አጥተው በእግራቸው ለመመለስ መገደዳቸውን ነው የገለጹት፡፡ በችግር ውስጥ ኾነው የተፈተኑ ተማሪዎችም የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥርባቸዋል ነው ያመላከቱት፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችም ፈተናውን ሳይፈተኑ መቅረታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት፣ የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ መንገድ ለመምራት እና በነጻነት ለመማር ሰላም አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለመሥራት አቅደው እንደነበር ያነሱት ኀላፊው በክረምቱ ወቅት የማካካሻ ትምህርት ለመስጠት፣ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገንና አረንጓዴ ለማድረግ አቅደው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በተፈለገው ልክ አለመሄዳቸውንም አመላክተዋል፡፡
ሰላም ካለ ልጆች ትምህርታቸውን በተገቢው መንገድ ይከታተላሉ፣ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ፣ ክልላቸውንና ሀገራቸውንም ይጠቅማሉ ነው ያሉት፡፡ የሰላም እጦቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ አድርጎብናልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!